የኢራን ፕሬዚዳንት በተቃዋሚዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ ቃል ገቡ  

ሰንደቅ ዓላማ እያቃጠሉ ያሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የኢራን ፕሬዝዳንት ከሳምንት በላይ ከዘለቀው የፀረ-መንግስት ሰልፎች በኋላ በተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል።

ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ወደ አብዛኞቹ የኢራን ግዛቶች የተዛመተውን ተቃውሞ “በቆራጥነት ለመፍታት” ቃል ገብተዋል።

ማህሳ አሚኒ ሂጃብ አልለበሽም በሚል በሞራል ደንብ አስከባሪ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ህይወቷ ማለፉን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ 35 ያህል ሰዎች መገደላቸውን ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ግጭቶችም በተለያዩ ከተሞች ቀጥለዋል።

ማህሳ የታሰረችው የሒጃብን ህግ ተላልፋለች በሚል ነው። ፖሊሶች መኪና ውስጥ በዱላ ጭንቅላቷን እየደበደቡና ከመኪና ጋር ማጋጨታቸው ተነግሯል። ፖሊስ ጉዳት ስለማድረሱ ምንም አይነት ማስረጃ እንደሌለ እና “ድንገተኛ የልብ ድካም" እንዳጋጠማት ተናግሯል።

ፕሬዚዳንት ራይሲ አሟሟቷ እንደሚጣራ ቢናገሩም፣ የሃገር ውስጥ ሚኒስትራቸው አህመድ ቫሂዲ በበኩላቸው ማህሳ እንዳልተደበደበች አስረግጠው ተናግረዋል።

“በተቆጣጣሪ አካላት ሪፖርቶች፣ በምስክሮች፣ በቪዲዮዎች፣ በፎረንሲክ ምርመራዎች ምንም ዓይነት ድብደባ እንዳልደረሰበት ተረጋግጧል" ብለዋል።

በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ እየተሰራጩ ያሉ ቪዲዮዎች ባለፉት ጥቂት ቀናት በሃገሪቱ በሚገኙ በደርዘን የሚቆጠሩ ከተሞች የተከሰቱ ሁከትና ብጥብጦችን አሳይተዋል።

አንዳንዶቹም በሰሜናዊ ምዕራብ በፒራንሻህር፣ ማሃባድ እና ኡርሚያ የጸጥታ ሃይሎች በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ጥይቶችን ሲተኩሱ አሳይተዋል።

ቅዳሜ ዕለት ርዕሰ መዲናዋ ቴህራን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ተጨማሪ ግጭቶች መከሰታቸው ተዘግቧል። ሰልፈኞች በአንድ ቦታ ላለመሰባሰብ እየተዘዋወሩ መሆናቸው ተነግሯል።

ተቃዋሚዎች በጸጥታ ሃይሎች ላይ የቤንዚን ቦንቦች ሲወረውሩ የሚያሳዩ አዳዲስ ምስሎችም በማህበራዊ ሚዲያዎች ታይተዋል።

ይህ በእንዲህእንዳለ የለውጥ አራማጆች የኢራን እስልምና ህዝቦች ፓርቲ አስገዳጅ የአለባበስ መመሪያው እንዲሰረዝ እና "ሰላማዊ ሰልፎች" እንዲፈቀዱ ጠይቀዋል። 

አምንስቲ ኢንተርናሽናል አሰባሰብኩት ባለው ማስረጃ “የኢራን የጸጥታ ሃይሎች ሆን ብለው በህገ-ወጥ መንገድ በተቃዋሚዎች ላይ ጥይቶችን የሚተኩሱበት አሰቃቂ ሁኔታ” መኖሩን ጠቁሞ አስጠንቅቋል።

የመንግስት ታጣቂዎች ረቡዕ ምሽት ብቻ 19 ሰዎችን በጥይት መግደላቸውን ገልጿል። ሦስቱ ህጻናት ናቸው። ቢቢሲ ይህንን በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻልም።

ራይሲ ተቃውሞውን “ሁከት” ሲሉ አጣጥለውታል። ኢራን "የሀገሪቱን ደህንነት እና ፀጥታ የሚቃወሙትን በቆራጥነት መያዝ አለባት" ብለዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች ተይዘው ታስረዋል። በሰሜን ምዕራብ በምትገኘው የጊላን ግዛት የፖሊስ አዛዡ ቅዳሜ ዕለት እንዳስታወቁት በክልላቸው ብቻ 60 ሴቶችን ጨምሮ 739 ሰዎች ታስረዋል።

ከታሰሩት መካከል የተወሰኑትን  ድብደባ ተፈጽሞብናል ማለታቸውን ቢቢሲ ሰምቷል። አንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ጋር ከመታሰሩ በፊት “በጭካኔ” ድብደባ እንደተፈፀመባቸው አንድ ግለሰብ ተናግሯል።  በታሰሩበትም ምግብ፣ ውሃ እና መታጠቢያ ቤት ማግኘት ተነፍገዋል።

እየተቃወሙ ያሉ ኢራናውያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የመንግሥት ሃይሎችም በገለልተኛ ሚዲያዎችና የህብረተሰብ አንቂዎች ላይ ዘመቻ ከፍተዋል። መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ ከሰኞ ጀምሮ 11 ጋዜጠኞች ታስረዋል ብሏል።

በድንበር ከተማዋ ኦሽናቪህ ተቃዋሚዎች የከተማዋን አንዳንድ ክፍሎች ከመንግስት ኃይሎች ለአጭር ጊዜ መቆጣጠራቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሰልፈኞች በአንድ ሌሊት እንደተቆጣጠሩ እና የጸጥታ ሃይሎች እና የመንግስት ባለስልጣናት ከሸሹበት ተመልሰው ቅዳሜ በድጋሚ ተቆጣጥረዋል ብለዋል።

ከከተማዋ የወጡ ቪዲዮዎች ብዙ ሰዎች በከተማው ጎዳናዎች ላይ ምንም ፖሊስ በሌለበት ሲጓዝ የሚያሳይ ሲሆን ከፍተኛ ፍንዳታም ይሰማል።