ዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ዕርዳታን ካቆመች ሺዎች ለሞት ይዳረጋሉ ተባለ

UK Soldier

የፎቶው ባለመብት, UK MoD

ታትሟል

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የሚሰጠውን እርዳታ የሚያቆም ከሆነ በአፍሪካ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ እናቶች እና ሕጻናት የመሞት አደጋ ይደቀንባቸዋል ተባለ።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ለውጭ አገራት ይሰጥ የነበረውን ዕርዳታ ለአጭር ጊዜ የማቋረጥ እቅድ አለው።

ይህ ግን በድሃ አገራት ላይ ቀላል የማይባል ጫና እንደሚያሳድር ሪፖርቶች እያመላከቱ ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ዕርዳታዋን ካቆመች ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ በተለይ በአፍሪካ ብዙ ሴቶች ለሞት እንደሚዳረጉ እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

አንድ የዳሰሰ ጥናትም በዚህ የዕርዳታ መቋረጥ ምክንያት በአፍሪካ ብቻ ቢያንስ 200 ሺህ ሴቶች የሕክምና አቅርቦት ባልተሟላ ሁኔታ ጽንስ ማቋረጥ ሊፈጽሙ ይችላሉ።

የውጭ ጉዳይ ቢሮ ለተወሰነ ጊዜ የውጭ ዕርዳታዎችን ለማቆም ማቀዱን አስታውቋል።

በአፍጋኒስታን የሚደረገው የ76 በመቶ የእርዳታ ቅነሳ ተጋላጭ ሴቶችን አደጋ ውስጥ እንደሚጥላቸው ተገልጿል።

በየመን ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን ሴቶች የጤና እንክብካቤያቸው ይቋረጣል።

ጥናቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ ዕርዳታውን ከማቋረጡ በፊት ለውሳኔ እንዲያግዝ ታሳቢ ተደርጎ የተሰራ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተደረገው የዳሰሳ ጥናት የውጭ ጉዳይ ቢሮ በዚህ ዓመት ይቀንሰዋል ተብሎ የሚጠበቀው ዕርዳታ በአጠቃላይ ከ900 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ የሚገመት ነው። ይህም የሆነው የውጭ ጉዳይ ቢሮው ቢያንስ ሩብ የሚሆነውን የውጭ ዕርዳታ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በቤት ልማት እንዲያውል ፈቃድ ማግኘቱን ተከትሎ ነው።

ነገር ግን በጀልባ እያቆራረጡ ወደ እንግሊዝ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። የእነዚህን ስደተኞች የሆቴል እና የቆይታ ወጭ መሸፈን ከፍተኛ ገንዘብ እየጠየቀ በመሆኑ ቢሮው ለውጭ እርዳታ የሚበጅተውን ገንዘብ እንዲቀንስ ያደርገዋል።

የእርዳታ ቅነሳው በተለያዩ አገራት ትላልቅ ተጽዕኖ የሚኖረው ሲሆን፣ በደቡብ ሱዳን እርዳታው የሚቀር ከሆነ 27 ሺህ ሕጻናት የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይገጥማቸዋል። ከእነዚህ መካከልም 12 በመቶ ወይም 3 ሺህ አካባቢ የሚሆኑት ለሞት እንደሚዳረጉ ቅድመ ጥናቱ ያስረዳል።

በዚህም ምክንያት የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ቢሮ የራሱን ወጭ በመቀነስ ወደ እነዚህ አገራት ተጨማሪ እርዳታ የሚልክበትን ሁኔታ ለመፍጠር አቅዷል። በዚህ ማዕቀፍ አፍጋኒስታን 41 ሚሊዮን ፓውንድ፣ የመን 32 ሚሊዮን፣ ሶሪያ 30 ሚሊዮን እና ሶማሊያ 30 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያገኙበት ሁኔታ ይፈጠራል ተብሏል።

በሚቀጥለው ዓመት ግን ዩናይትድ ኪንግደም ለአፍሪካ የምታደርገው ድጋፍ በእጥፍ ይጨምራል ተብሏል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ቢሮ ቃል አቀባይ በሚቀጥለው ዓመት ለውጭ ዕርዳታ የሚውለው በጀት 8.3 ቢሊዮን ፓውንድ እንደሚሆን ገልጸዋል። በዋናነትም ይህ ገንዘብ ሰብዓዊ ቀውስ፣ ሴቶችና ተጋላጭ ሰዎችን ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።

ቃል አቀባዩ “የቁጠባ ግባችንን ለመሙላት በዚህ ዓመት የውጭ ዕርዳታዎችን ለአጭር ጊዜ ብናቆምም በሚቀጥለው ዓመት ግን አገራት እጥፍ ሊባል በሚችል ደረጃ ድጋፍ ያገኛሉ” ብለዋል።

በዚህ መነሻም 646 ሚሊዮን ፓውንድ የነበረው የአፍሪካ ድጋፍ ወደ 1.364 ቢሊዮን ፓውንድ እንደሚያድግ ገልጸዋል።