እስራኤል ሦስት የሄዝቦላህ ድሮኖችን ጣለች

በሜዲትራኒያን የሚገኘው የእስራኤል የጋዝ ክምችት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የእስራኤል ባለሥልጣናት የሔዝቦላህ ሦስት ድሮኖችን መትተው መጣላቸውን አስታወቁ።

ድሮኖቹ ወደ ሜዲትራኒያን የእስራኤል የጋዝ ክምችት ማውጫ ላይ ጉዳት ለማድረስ ያመሩ የነበሩ ናቸው።

እንደ ባለሥልጣናቱ ከሆነ ድሮኖቹ የተነሱት ከሊባኖስ ሲሆን ተመትተው የተጣሉት ደግሞ በተዋጊ ጄቶችና ከመርከብ በተጠመዱ የእስራኤል ሚሳኤሎች ቅንጅት ነው።

ሔዝቦላህ ድሮኖቼ ተመተውብኛል ባይልም ድሮን ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር መተኮሱን ግን በአጭር መግለጫ አምኗል።

በእስራኤልና ሊባኖስ መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፍጥጫው እየተካረረ መጥቷል።

ይህም በሜዲትራኒያን የጋዝ ክምችት ሥፍራ የይገባኛል ጥያቄ የተነሳ ነው።

በሜዲትራኒያን ባሕር ካሪሽ የሚባል የጋዝ ክምችት ሥፍራ ሁለቱም አገሮች ይገባኛል ያነሱበታል።

የአሜሪካ የኢነርጂ ጉዳዮች ልዩ መልእክተኛ አሞስ ሆሽቴይን እስራኤልንና ሊባኖስን በዚህ ጉዳይ ለማግባባት እየሞከሩ ይገኛሉ።

እስራኤል ይህ የባሕር የጋዝ ክምችት የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት እውቅና በሰጠኝ የኢኮኖሚ ክልል ነው፤ ስለዚህ የኔ ነው ትላለች።

ሊባኖስ በበኩሏ ከፊሉ ለኔ ይገባል ትላለች።

ሔዝቦላህ ሦስቱን ድሮኖች የላኩት መረጃ እንዲቃርሙልኝ ነበር መረጃውንም ደርሶኛል፤ ያለምኩትም ተሳክቷል ብሏል።

ባለፈው ሳምንት የሔዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህ ይህን የጋዝ ክምችት ሥፍራ እስራኤል የምታለማው ከሆነ ጥቃት እንሰነዝራለን ብለው ዝተው ነበር።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ይህ ጽንፈኛ ቡድን የሊባኖስ መንግሥት ከሰላማዊ  የባሕር ድንበር ስምምነት ተጠቃሚ እንዳይሆን እያደረገ ነው ሲሉ ከሰዋል።

የሊባኖስ አገር ከምንጊዜም በላይ ብልጽግናና እድገትን በሚሻበት ጊዜ ሔዝቦላህ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል ሚኒስትሩ።

የሔዝቦላህ የድሮን ጥቃት ሙከራ የተደረገው በእስራኤል የመንግሥት አለመርጋት ባጋጠመበት ማግስት ነው።

ባለፈው ሐሙስ ሕግ አውጪዎች በ4 ዓመት ውስጥ ለ5ኛ ጊዜ ምርጫ እንዲካሄድ በሚል መበተናቸው ይታወሳል።

የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ባኔት የሚመሩት የጥምር መንግሥት ተንገዳግዶ ከፈረሰ በኋላ የቀኝ ዘመሙ ፓርቲ መሪ ቤኒያሚን ናታንያዩ በድጋሚ ወደ ሥልጣን የሚመጡበት ዕድል ተከፍቶላቸዋል።

ናታኒያሁ እስራኤልን ለበርካታ ዓመታት የመሩ ናቸው።