ዩክሬን በሳምንታት ውስጥ ሌላ የሩሲያን የስለላ አውሮፕላን መትታ መጣሏን አስታወቀች

ታትሟል

ዩክሬን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ኤ-50 የተባለ የሩሲያን የጦር የስለላ አውሮፕላን መትታ መጣሏን አስታወቀች።

የዩክሬን የጦር ምንጮች እንደተናገሩት አውሮፕላኑ ተመትቶ የወደቀው ከጦር ግንባር በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሮስቶቭ ኦን ዶን እና በክራስኖዳር ከተሞች መካከል በሚገኝ ቦታ ላይ ነው።

በአካባቢው የነበሩ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ሰጪዎች በካንቭስኮይ አካባቢ የአውሮፕላን ስብርባሪ ማግኘታቸውንና የተያያዘውን እሳት ማጥፋታቸውም ተዘግቧል።

ሩሲያ ስለክስተቱ የሰጠችው አስተያየት የለም።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ከጀመረች ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 16/ 2016 ዓ.ም ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል።

የዩክሬን አየር ኃይል አዛዥ ሚይኮላ ኦሌሽቹክ አርብ ዕለት አውሮፕላኑን መጥቶ ለመጣል የረዱትን መሥሪያ ቤታቸውንና እና የጦር ደኅንነት አካላትን አመስግነው ክስተቱም ከሩሲያ ወታደራዊ በዓል ጋር መገጣጠሙን ገልጸዋል።

በበይነ መረብ የተጋራ ተንቀሳቃሽ ምስል አውሮፕላኑ በአየር ላይ ሲመታና በእሳት ሲቀጣጠል ከዚያም መሬት ላይ ከወደቀ በኋላ ጥቁር ጭስ ሲወጣ አሳይቷል።

በኋላ ላይም የክራስኖዳር የድንገተኛ አገልግሎት ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ በካንቭስኮይ ወረዳ፣ በትሩዶቫያ አርመኒያ መንደር መከስከሱንና በእሳት መያያዙን ገልጸዋል። ሆኖም ስለ ክስተቱ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ከሩሲያ ጦር ጋር ግንኙነት ያለው የቴሌግራም ገጽ አውሮፕላኑ ከራሱ ወገን ባጋጠመው አደጋ ሊከሰከስ እንደቻለ ጠቁሟል።

ፋይተርቦምበር የተባለው የቴሌግራም ገጽ “ በወቅቱ አውሮፕላኑን ማን እንደመታው አልታወቀም” ብሏል።

ዩክሬን የሩሲያን ኤ -50 የተባለ አውሮፕላን መጥታ መጣሏን ለመጨረሻ ጊዜ ያስታወቀቸው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ሲሆን በአንድ ወር ውስጥ ተመሳሳይ አውሮፕላን መትታ መጣሏን ስትገልጽ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት በሰጠው መግለጫ ሩሲያ በአገልግሎት ላይ ያሉ ስድስት ኤ-50 አውሮፕላኖች እንደነበሯት ገልጾ ነበር።

ኤ-50 የተሰኘው ስለላ አውሮፕላን የአየር መከላከያዎችን በመለየት የሩስያ ጄቶች ዒላማዎችን እንዲያጠቁ የሚያመቻች ሲሆን ይህን አውሮፕላን ለመስራት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ያስወጣል።

ዩክሬን በደቡብ ምስራቅ የሩሲያ ኃይሎችን ግስጋሴ ለመግታት እየታገለች ነው።

ባለፈው ወር የአገሪቷ የጦር ባለሥልጣናት የሩሲያን ኤ-50 የተሰኘ በረዥም ርቀት ራዳር የሚቃኝ የስለላ አውሮፕላን እና አይኤል-22 የተሰኘ የቁጥጥር ማዕከል አውሮፕላንን ማውደሟን መግለጻቸው ይታወሳል።