ፕሬዝዳንት ባይደንን ለመግደል ሲዝት የነበረው ሰው በኤፍቢአይ ተገደለ

Utah

የፎቶው ባለመብት, google

ታትሟል

ሮበርትሰን ይባላል። ነዋሪነቱ በአሜሪካ ኡታህ ነው።

ይህ ግለሰብ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ሌሎች ባለስልጣናት ላይ ከፍተኛ ዛቻዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ በማጋራት ይታወቃል።

ይህ ተግባሩ ግን ሕልውናውን አሳጥቶታል። ትናንት [ረቡዕ] ኤፍቢአይ ባደረገው አሰሳ ግለሰቡ በጥይት ተመትቶ መገደሉ ታውቋል።

ሮበርትሰን በፌስቡክ ገጹ ባጋራው መልዕክት ፕሬዝዳንት ባይደን እና በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዙሪያ የወንጀል ክስ በሚመሰርተው ዓቃቤ ሕግ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽም ሲዝት ነበር።

ነገር ግን ሰውየው ምንም አይነት ተግባራዊ ርምጃ ከመውሰዱ በፊት በበፌደራሉ የምርመራ ቢሮ ፣ኤፍቢአይ ተገድሏል።

ስለአገዳደሉ ኤፍቢአይ የሰጠው ዝርዝር ነገር የለም።

ሮበርትሰን በፌስቡክ ገጹ የጠመንጃ እና የሽጉጥ ምስሎችን በተደጋጋሚ በማጋራት፣ ፕሬዝዳንት ባይደንን እና የማንሃተን ግዛት ዓቃቤ ሕግ የሆኑትን እና በዶናልድ ትራምፕ ላይ ክስ ያዘጋጁትን አልቪን ብራግን እንደሚገድላቸው ሲዝት ነበር።

በተዘጋጀበት የወንጀል መዝገብ ላይ እንደተሰነደው ሮበርትሰን ሌሎች ዓቃቤ ሕጎችንም እንደሚገድል የሚገልጹ መልዕክቶች ተገኝተዋል።

“ባይደን ወደ ኡታህ እየመጣ መሆኑን ሰምቻለሁ። ተዘጋጅቼ እና 'ስናይፐሬን' [አነጣጥሮ ተኳሽ ጠመንጃዬን] ወልውዬ እጠብቀዋለሁ” በማለት ነበር ሮበርትሰን መልዕክቱን በፌስቡክ ገጹ ያጋራው።

ሮበርትሰን በሚጠቀምባቸው ሁለት የፌስቡክ ገጾች ከሚጋሩ በርካታ የማስፈራሪያ መልዕክቶች ይህ አንደኛው ነው።

ኤፍቢአይ ጉዳዩን በጥብቅ መከታተል የጀመረው ትሩዝ ተብሎ በሚጠራው የዶናልድ ትራምፕ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ በማንሃተን ዓቃቤ ሕግ አልቪን ብራግ ላይ የማስፈራሪያ መልዕክት ሲያጋራ ነው።

የጉዳዩን አደገኛነት ተከትሎ የትሩዝ ኩባንያ የሮበርትሰንን ድርጊት ለኤፍቢአይ ጠቁሟል።

ይህንን ተከትሎ የኤፍቢአይ ሰዎች ሮበርትሰን ጋ በመሄድ ጥያቄ ያቀርቡለታል።

ሮበርትሰን ግን ይህ የሚኖርለት ሕልሙ መሆኑን ገልጾ “ለአሁኑ ጨርሰናል። ወደፊት ግን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳትመለሱ” ብሎ ሸኛቸው።

ከዚያ በኋላ ከኤፍቢአይ ሰዎች ጋር ያደረገውን ንግግር እንደጀብዱ በመቁጠር ራሱን እንደ ጀግና በመሳል መሣሪያዎችን እየተሸከመ የሚነሳቸውን ፎቶዎች መለጠፉን ቀጠለ።

ሮበርትሰን እስከባለፈው ማክሰኞ ድረስ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው መልዕክቶችን ማጋራቱን ቀጥሎ ነበር። ማክሰኞ ያጋራው መልዕክት ደግሞ “ይህ ስናይፐር ባይደንን አነጣጥሮ ስለሚመታ ኡታህ እንደቦታ ዝናዋ ይናኛል” የሚል መልዕክት ነበር ያጋራው።

ነገር እን ኤፍቢአይ ሰውየውን ቀድመው ገድለውታል።

ጆ ባይደን ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ኡታህን ዛሬ [ሐሙስ] ይጎበኛሉ።