አስራኤል ከግብፅ ጋር በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ ሦስት ወታደሮቿ ተገደሉ

እስራኤል ከግብፅ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር በኩል ዕጽ አዘዋዋሪዎች ጥቃት ይፈጽማሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል ከግብፅ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር በኩል ዕጽ አዘዋዋሪዎች ጥቃት ይፈጽማሉ
ታትሟል

ከግብፅ ድንበር አቅራቢያ ሦስት የእስራኤል ወታደሮች በአንድ ታጣቂ ሲገደሉ ሌሎች መቁሰላቸውን የእስራኤል ጦር ሠራዊት አስታወቀ።

ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት በታጣቂው በተሰነዘረው ጥቃት ሴት እና ወንድ ወታደሮች ናቸው የተገደሉት። አስከሬናቸው የተገኘውም ሌላ መኮንን በሬዲዮ ሊያገኛቸው ሞክሮ ሳይሳካለት ከቀረ በኋላ ነው።

ጥቃቱን ፈጥሟል የተባለው ታጣቂ በኋላ ላይ መገደሉ የተነገረ ሲሆን፣ ሦስተኛው የእስራኤል ወታደር የተገደለው ደግሞ ጥቃት ፈጻሚውን ለማግኘት በተካሄደ አሰሳ ወቅት ነው።

ይህ በአስራኤል ወታደሮች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ያጋጠመው በድንበር አካባቢ የተደረገ የአደገኛ ዕጽ አዘዋዋሪዎች እንቅስቃሴ በቁጥጥር ስር ከዋለ ከሰዓታት በኋላ ነው።

የእስራኤል ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ኮሎኔል ሪቻርድ ሄሼት እንዳስታወቁት የአደገኛ ዕጽ አዘዋዋሪዎች መሰላል በመጠቀም በድንበር አጥር በኩል ሊያሸጋግሩት የነበረ 400 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ዕጽ ተይዞባቸዋል።

የአደገኛ ዕጽ አዘዋዋሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋል ኋላ ላይ በወታደሮቹ ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር የተያያዘ ነው ተብሎ ተገምቷል።

ጥቃቱን የፈጸመው ታጣቂ ማንነትን በተመለከተ የተጠየቁት የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ፣ የኢስላሚክ ስቴት አባል፣ የድንበር ጠባቂ ወይም የዕጽ አዘዋዋሪ ሊሆን እንደሚችል በመጥቀስ “ማንነቱን ለመለየት ጥረት እያደረግን ነው። ነገር ግን እስካሁን ማንነቱ ግልጽ አይደለም” ብለዋል።

የእስራኤል ጦር ሠራዊት ክስተቱን በሚመለከት ባወጣው መግለጫ “ከግብፅ ጦር ሠራዊት ጋር ሙሉ ለሙሉ በመተባበር በጥቃቱ ዙሪያ ምርመራ ተደርጓል” ብሏል።

በእስራኤል የድንበር አካባቢ ከሚዘዋወረው አደገኛ ዕጽ በተጨማሪ የፍልስጥኤም ታጣቂ ቡድኖች ሰርገው በመግባት ጥቃት የሚፈጽሙ ሲሆን፣ የጦር መሳሪያዎችን ለማዘዋወርም ይጠቀሙበታል።