ዩክሬን በመልሶ ማጥቃት በዶኔስክ ግዛት ሦስት መንደሮች ነጻ አወጣሁ አለች

ታትሟል

ዩክሬን በሩሲያ ጦር ላይ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ማካሄድ ከጀመረች በኋላ በዶኔስክ ግዛት በሩሲያ ይዞታ ስር ገብተው የነበሩ ሦስት መንደሮችን ነጻ ማውጣቷን ገለጸች።

ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተጋሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ የዩክሬን ወታደሮች ነጻ ባወጧቸው ብላሆዳንቴ እና ኔስኩችን በተባሉ አካባቢዎች ደስታቸውን ሲገልጹ አሳይቷል።

የዩክሬን ምክትል መከላከያ ሚንስትር በአቅራቢያ ያለችው ማካሪቭካ የተባለች ሦስተኛ መንደር በሠራዊታቸው እጅ መግባቷን ተናግረዋል።

ዩክሬን በሩሲያ ጦር ላይ እፈጽመዋለሁ ብላ ስትዘጋጅበት የቆየችው እና ብዙ የተጠበቀው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ መጀመሩን የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ትናንት እሁድ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ፕሬዝዳንቱ ማረጋገጫ ከመስጠታቸው በፊት ዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻዋን ስለመጀመሯ መረጃዎች ሲወጡ ነበር።

ሞስኮ እነዚህ መንደሮች በዩክሬን እጅ ስለመግባታቸው እስካሁን ያለችው ነገር የለም፤ ይሁን እንጂ የዩክሬንን መልሶ ማጥቃት እያከሸፈች እንደሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።

በሌላ አካባቢ እየተደረገ ባለ ጦርነት ደግሞ ሩሲያ በዛፖሬዢያ ያለ ሌላ ግድብ ማፈንዳቷን ዩክሬን ገልጻለች።

ባለፈው ሳምንት ሩሲያ ቮቫ ካህኮቭካ የተባለ ግድብ ማውደሟን ተከትሎ የተፈጠረው የውሃ መጥለቅለቅ 596 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታን የሸፈነ ሲሆን፣ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ማድረጉን ዜሌንስኪ ተናግረው ነበር።

ይህ በዛፖሬዢያ ግዛት ያለው ግድብ እንዲፈነዳ የተደረገው በሩሲያ ወታደሮች መሆኑን እና ግድቡ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ የዩክሬን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

የዩክሬን ጦር ቃል አቀባይ የሆኑት ቫሌሪይ ሼርሼን ሞስኮ ሆነ ብላ ግድቦችን እያወደመች ያለችው በውሃ መጥለቅለቅ የዩክሬን ጦር የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴን ለመገደብ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ኦፕሬሽን ከመጀመርኩ በኋላ ተቆጣጥሪያቸዋለሁ ያለቻቸው መንደሮች አነስተኛ ሕዝብ ይኖርባቸው የነበሩ ቢሆንም ከፍተኛ ውጊያን ያስተናገዱ አካባቢዎች ናቸው።

ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ ትናንት አገራቸው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ መጀመሯን ይፋ ሲያደርጉ ዝርዝር ዕቅዳቸውን በተመለከት መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የሩሲያ እና የዩክሬንን ጦርነት በቅርብ የሚከታተሉ ተንታኞች ግን የዩክሬን ዓላማ በሩሲያ ሥር የገቡት ክሬሚያ እና ዶኔስክ የሚያገናኘውን ድልድይ በመቆጣጠር የሩሲያን ጦር ሁለት ቦታ መቁረጥ ነው።

በምሥራቅ ዩክሬን እየተደገረ ባለው ጦርነትም የዩክሬን ወታደሮች ከፍተኛ ውጊያ በተደረገባት ባኽሙት አቅራቢያ ወደፊት እየገፉ ስለመሆኑ ተሰምቷል።

ዩክሬን በሩሲያ ጦር ላይ የከፍተችው ዘመቻ ስፋት ግልጽ ባይሆንም መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ‘ስተዲ ኦፍ ዋር’ የተባለ ተቋም፣ ኪዬቭ ቢያንስ በአራት አቅጣጫዎች በሞስኮ ላይ የመልሶ ማጥቃት ጦርነት ከፍታለች ብሏል።

ዩክሬናውያኑ ሊዮፓርድ 2 የተሰኙ የጀርመን ታንኮችን በማሰማራት የሩሲያ ምሽግ መስበር የቻሉባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውም ተመላክቷል።