ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካዊው ቱጃር ጆርጅ ሶሮስ 25 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብታቸውን ለልጃቸው አወረሱ
ከዩናይትድ ስቴትስ ቀንደኛ ቢሊየነሮች አንዱ የሆኑት ጆርጅ ሶሮስ 25 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብትና የተራድዖ ድርጅትን ኃላፊነት ለልጃቸው አስረክበዋል።
ሃንጋሪ የተወለዱት የፋይናንስ ባለሙያው ሶሮስ ከዎል ስትሪት ጆርናል ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ልጄ አሌክስ ሃብት እና ኃላፊነቱ “ይገባዋል” ብለዋል።
ከ1990ዎቹ ጀምሮ የቤተሰቡ ሃብት በተለያዩ ሃገራት ዴሞክራሲን ለመገንባት ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የ92 ዓመቱ ቱጃር የፀረ-ሴሜቲክ የሤራ ትንታኔዎች ትኩረት ሆነዋል።
ጆርጅ ሶሮስ ለጆ ባይደኑ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ወፍራም የገንዘብ እርዳታ በማድረግ ይታወቃሉ።
የ37 ዓመቱ አሌክስ ኮሌጅ ገብቶ ታሪክ ያጠና ሲሆን ከአምስቱ የሶሮስ ልጆች ሁለተኛ ልጅ ነው።
አሌክስ፤ የሶሮስ ኢንቨስትመንት ፈንድ ውስጥ ካለው ኮሚቴ ውስጥ የተካተተ ብቸኛው የቤተሰብ አባል ሲሆን ዎል ስትሪት ጆርናል እንደሚለው ይህ ኮሚቴ 25 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የቢዝነስና የእርዳታ ሥራን የሚዘውር ነው።
ባለፈው መስከረም አሌክስ፤ ኦፕን ሶሳይቲ ፋውንዴሽን የተባለው ድርጅትና አባቱ ሶሮስ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እርዳታ የሚያደርጉበት ሱፐር ፓክ የተባለው ተቋም ኃላፊ ሆኖ ብቅ ብሏል።
የአባቱን አድማስ የሚሻገር ሃብት የወረሰው አሌክስ ከአባቱ ጋር የሚመሳሰል ፖለቲካዊ አቋም ቢኖረውም እሱ የበለጠ ፍላጎት እንዳለው ይናገራል።
አሌክስ፤ ዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛ ጊዜ አሜሪካን እንዳይመሩ ቅስቀሳ ማድረግ እንደሚጀምርም ገልጧል።
“ገንዘብና ፖለቲካ እንዳይደባለቁ ፍላጎት ቢኖረኛም፤ ሌላኛው ወገን እስካደረገው ድረስ እኛም ልናደርገው ይገባል።”
አባቱ ጆርጅ ሶሮስ የተወለዱት ሃንጋሪ ነው። በፈረንጆቹ ከ1944-45 ናዚዎች ሲገቡ እሳቸውና ቤተሰቦቻቸው የአይሁድ ማንነታቸውን ደብቀው ተርፈዋል።
ከጦርነቱ በኋላ ከሃንጋሪ ወደ ለንደን አቀኑ። ቀጥሎም ወደ ኒው ዮርክ። ከዚያ በኋላ ነው በፋይናንስ መስክ ቢሊዮኖች ማፈስ የጀመሩት።
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ እውቅና ያገኙት በ1992 ፓውንድ [መገበያያ ገንዘብ] ይወድቃል ብለው መድበው 1 ቢሊዮን ዶላር ከበሉ በኋላ ነው።
ኦፕን ሶሳይቲ ፋውንዴሽን በየዓመቱ 1.5 ቢሊዮን በማፍሰስ በ120 ሃገራት በላይ የትምህርትና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንዲጎለብቱ ይሠራል።
ቡዳፔስት የነበረው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት የሃንጋሪ መንግሥት ጆርጅ ሶሮስ ላይ ተቃውሞ በማንሳቱ ምክንያቱ ወደ በርሊን ተዛውሯል።
አሌክስ ሶሮስ ሂፕ ሆፕ የተሰኘው የሙዚቃ ዘውግ አድናቂ ሲሆን፤ ኒው ዮርክ ጄትስ የተባለው ‘የአሜሪካ እግር ኳስ’ ቡድን ቀንደኛ ደጋፊ ነው።
አልፎም የተለያዩ ፓርቲዎችን በመታደም እንዲሁም ፌስቲቫሎች ላይ በመገኘት ይታወቃል።