ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዜሌንስኪ ጦራቸው የያዛቸውን የሩሲያ አካባቢዎች እያጠናከረ ወደፊት እየገፋ ነው አሉ
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ ጦራቸው የተቆጣጠራቸውን የሩሲያ አካባቢዎች “እያጠናከረ” ወደፊት እየገሰገሰ ነው ሲሉ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ይህን ያሉት የዩክሬን ጦር የሩሲያን ድንበር ተሻግሮ ኩርስክ ወደተባለው የሩሲያ ክልል ከገባ ሁለት ሳምነት ካለፈው በኋላ ነው።
ፕሬዝዳንቱ የዩክሬን ጦር በየዕለቱ በግዛቷ ወደፊት እየገፉ ነው ብለዋል።
ሞስኮ በዩክሬን የተፈጸመባትን ጥቃት “ትልቅ ጠብ የሚጨር ወረራ” ብላ ከገለጸች በኋላ አግባብ የሆነ ምላሽ ይሰጠዋል ብላለች።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በቴሌግራም ገጻቸው ለዩክሬን ሠራዊት አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሩሲያን ወታሮች እና የጦር አዛዦች በመያዝ የዩክሬን ወታደሮች እና ሰላማዊ ሰዎች ነጻ እያወጡ ላሉ የሠራዊት አባላት ምስጋና አቅርበዋል።
የሩሲያ ጦር በበኩሉ በኩርስክ ግዛት ሦስት የመኖሪያ መንደሮችን ለመቆጣጠር ጥረት ያደረገ የዩክሬን ጦርን መምታቱን አስታውቆ በግዛቷ ወደፊት ለመግፋት ጥረት እያደረገ ያለ ተንቀሳቃሽ የጠላት ኃይልን እየተከታተልን ነው ብሏል።
ኪዬቭ በዚህ ወታደራዊ ዘመቻ በኩርስክ ግዛት ከ90 ያላነሱ የመኖሪያ አካባቢዎችን መቆጣጠሯን ትገልጻለች።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የተቆጣጠርናቸውን የሩሲያ አካባቢዎች አጠናክረን ይዘናል የሚለውን መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የዩክሬን ጦር ሩሲያ ውስጥ የሚገኝ ቁልፍ የሆነ ድልድይ ማውደሙ ከተገለጸ በኋላ ነው።
ሩሲያ ወደ ድንበሯ ዘልቆ የገባውን የዩክሬን ጦር ለመመከት ለሎጂስቲክ አቅርቦት የምትጠቀምበትን እና ሰየመ የተባለ ወንዝን የሚያሻግር ግዙፍ ድልድይ በዩክሬን ከቀናት በፊት ወድሟል።
የሩሲያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ድልድዩ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ገልጾ፤ ሰላማዊ ሰዎችን ከጦር ቀጠና ለማውጣት ሲሰሩ የነበሩ በጎ ፍቃደኞች ተገድለዋል ብሏል።
የዩክሬን ጦር ወደ ምዕራብ ሩሲያ ገብታ አካባቢዎች መቆጣጠሯን ብትቀጥልም የሩሲያ ጦር ደግሞ በምስራቃዊ ዩክሬን አዳዲስ አካባቢዎችን መያዙን ቀጥሏል።
ትናንት ቅዳሜ ሩሲያ ቢያንስ በአራት የዩክሬን ግዛቶች ላይ ከባድ ጥቃት ከፍታ በርካታ አካባቢዎችን መያዟ ተነግሯል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ እንዲሁ በምስራቅ ዩክሬን በሚገኙ አካባቢዎች ከባድ የሩሲያ ጥቃት መፈጸሙን ተናግረው ጦራቸው የሩሲያን ጥቃት ለመመከት የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው ብለዋል።