የግዙፍ ሚዲያዎች ባለቤት የሆኑት ሩፐርት መድሮክ በቲክቶክ ግዢ ላይ ሊሳተፉ እንደሚችሉ ትራምፕ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ፎክስ ኒውስ እና ዎል ስትሪት ጆርናልን ጨምሮ የበርካታ መገናኛ ብዙኃን ባለቤት የሆኑት ሩፐርት መርዶክ እና ልጃቸው ላችላን በአሜሪካ ቲክቶክን ከሚገዙ ኢንቨስተሮች መካከል ሊሆኑ እንደሚችሉ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።
ትራምፕ እሁድ ዕለት ከፎክስ ቲቪ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ፤ ሰዎቹ "ምናልባት" ቲክቶክ አሜሪካ ውስጥ እንዲቆይ በቀረበው ምክረ ሃሳብ ላይ ተሳትፈው ሊሆን ይችላል ብለዋል።
አክለውም የኦራክል ሊቀመንበር የሆኑት ላሪ ኤሊሰን እንዲሁም የዴል መስራቹ ማይክል ዴል እንዲሁ ሊሳተፉ እደሚችሉ ተናግረዋል።
"ጥሩ ሥራ የሚሰሩ ይመስለኛል" ያሉት ዶናልድ ትራምፕ፤ ግሰለቦቹን "አሜሪካዊ አርበኞች" ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።
ባለፈው ሳምንት ከቻይና አቻቸው ጋር ውይይት ያደረጉት ፕሬዚዳንቱ፤ አሜሪካ እና ቻይና የማኅበራዊ ሚዲያው በአሜሪካ ለዩኤስ ባለሀብቶች እንዲሸጥ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረው ነበር።
ቲክቶክ የሚሸጠው፤ እአአ በ2024 ሚያዚያ ወር በኮንግረስ የጸደቀው ሕግ የማኅበራዊ ሚዲያውን በባለቤትነት የያዘው የቻይናው ባይትዳንስ በአሜሪካ ያለውን እንቅስቃሴ ለአገሪቱ ባለሀብቶች ካልሸጠ እንዲታገድ በማለቱ ነው።
ሕጉ የጸደቀው ቻይና የ170 ሚሊዮን አሜሪካውያን የቲክቶክ ተጠቃሚዎችን የግል መረጃን ልትጠቀምበት ትችላለች በሚል ፍራቻ ነው። እስካሁን ድረስ ሕጉ ተፈጻሚ ሳይሆን ቆይቷል።
በቲክቶክ ስምምነት ወቅት ምክረ ሃሰብ በማቅረብ እነማን እንደተሳተፉ ጥያቄ የቀረበላቸው ትራምፕ "በጣም የሚታወቁ ሰዎች ናቸው"፤ "ከፍተኛ መጠን ያለው" ገንዘብ ሊያሰባብሱ የሚችሉ ናቸው ብለዋል።
"ላሪ ኤሊሰን አንዱ ነው። እርሱ ተሳትፏል፣ ያ ግሩም ሰው ማይክል ዴልም ተሳትፏል። ይህንን ስነግራችሁ እጅግ በመደሰት ነው ላችላንም እዚህ ውስጥ ተሳትፏል። ላችላን ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ?" ብለዋል።
"ሩፐርት ምናልባት በዚህ ቡድን ውስጥ ሊካተት ይችላል" ብለዋል።
ላችላን መርዶክ የቤተሰቡ ንብረት የሆነውን ግዙፉን የሚዲያ ተቋም ከወንድም እና እህቶቹ ጋር የተራዘመ ፍርድ ቤት ክርክር ካደረገ በኋላ ጠቅልሎታል።
የ94 ዓመቱ ሩፐርት መርዶክ የኤሜሬትስ ኦፍ ኒውስ ኮርፖሬሽን ሊቀመንበር ናቸው።
እሁድ ዕለት ትራምፕ አስተየየት ከሰጡ በኋላ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን መርዶክ በግሉ ኢንቨስት እንደማያደርግ ከዚያ ይልቅ በፎክስ ኮርፖሬሽን በኩል ግዢውን አንደሚፈጽም ዘግበዋል።
የመርዶክ ግዙፍ የሚዲያ ኩባንያዎች በወግ አጥባቂ አመለካከታቸው እና ቀኝ ዘመም በሆነው የሚዲያ ሥራዎቻቸው የሚታወቁ ሲሆን ዋል ስትሪት ጆርናል እና ፎክስ ኒውስን በባለቤትነት ያስተዳድራሉ።
የመርዶክ የሚዲያ ኩባንያዎች አልፎ አልፎ ትራምፕን የሚያስቆጡ ዘገባዎች የሚሰሩ ሲሆን በቅርቡም ዎል ስትሪት ጆርናል ትራምፕ የጄፍሪ ኢፕስታይን የልደት ማስታወሻ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል በማለቱ በስም ማጥፋት ወንጀል ከስሰውታል።
አሜሪካ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ቲክቶክ; ከቻይናው ባይትዳንስ እጅ እንዲወጣ ግፊት በጨመረበት በአሁኑ ወቅት ዋይት ሐውስ ስምምነቱ ወደ መጠናቀቁ መሆኑን አስታውቋል።
ቅዳሜ ዕለት የዋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ ካሮላይን ሌቪት ስምምነቱ "በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ" ይፈረማል ብለዋል።
ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራት ቃለምልልሰ ላይ ቪዲዮ እየመረጠ ለተጠቃሚዎች የሚያቀርበውን የቲክቶክ አልጎሪዝም የአሜሪካ ኩባንያዎች እንደሚቆጣጠሩት ተናግራለች።
ከቻይና ጋር በሚደረገው ድርድር የመተግበሪያው የአሜሪካ እንቅስቃሴን በተመለከተ ከሰባቱ የቦርድ አባላት ስድስቱ አሜሪካውያን እንደሚሆኑም ስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግራለች።
ቅዳሜ ዕለት የቻይና ንግድ ሚኒስቴር የስምምነቱን ሁኔታ በሚመለከት ግልፅ ያልሆነ መግለጫ አውጥቷል።
"በቲክቶክ ጉዳይ የቻይና አቋም ግልፅ ነው። የቻይና መንግሥት የኩባንያውን ፍላጎት ያከብራል። የቻይናን ሕግ እና ደንብ እና የጥቅም ሚዛንን ባከበረ መልኩ መፍትሔ ላይ ለመድረስ የሚያደርገውን የንግድ ስምምነት ይቀበላል" ብሏል።
የቻይና ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን የሆነው ዥንዋ የድርድሩን ውጤት በተመለከተ ግልፅ ያልሆነ ዘገባ ያወጣ ሲሆን፤ ዘገባው የፕሬዝዳንትን ዢን ንግግር በመጥቀስ ቤጅንግ "የቲክቶክ ድርድርን ትቀበላለች" ብሏል።
ባይትዳንስ እስካሁን ድረስ ትራምፕ በሰጡት አስተያየት ላይ አቋሙን አላሳወቀም።















