ዩናይትድ ኪንግደም አንዳንድ የጦር መሣሪያዎች ለእስራኤል እንዳይሸጡ አገደች

የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዩኬ ለእስራኤል የምትሸጣቸው አንዳንድ የጦር መሣሪያዎች ዓለም አቀፍ ሕግ የሚጥስ ተግባር ሊፈፅማባቸው ስለሚችል በሚል ሽያጯን መግታቷን አስታውቃለች።

የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ሀገራቸው ወደ እስራኤል ከምትልካቸው 350 የጦር መሣሪያዎች መካከል 30 የሚሆኑትን አግዳለች ብለዋል።

ወደ እስራኤል እንዳይላኩ ከታገዱት የጦር መሣሪያዎች መካከል የጦር አውሮፕላኖች፣ ሄሊኮፕተሮች እና ድሮኖች ይገኙበታል።

አንድ የእስራኤል ባለሥልጣን የዩኬ ውሳኔ “የተሳሳተ መልዕክት የሚያስተላልፍ እና የሚያበሳጭ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሚኒስትር ላሚ፤ እስራኤል ራሷን የመከላከል መብቷን ዩኬ ትደግፋለች ብለው ይህ ውሳኔ የጦር መሣሪያ ማዕቀ ብ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት አሳስበዋል።

የእስራኤል የዳያስፖራ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አሚቻይ ቻክሊ ይህ ውሳኔ እስራኤል በሐማስ ታግተው የተገደሉባት ስድስት ዜጓችን እየቀበረች ባለች ወቅት መሆኑ “ስሜታዊ” ያደርገዋል ብለዋል።

“ከኢስላሚክ ስቴት ግሩፕ፣ ከአል-ቃዒዳ እና ሐማስ ጋር የሚደረገው ጦርነት ተመሳሳይ ነው። ይህ ጦርነት በምዕራባዊ ሥልጣኔ እና በአክራሪ ኢስላም መካከል የሚደረግ ነው” ብለዋል።

የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ውሳኔውን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት ሀገራቸው ዓለም አቀፍ ሕግን ተከትላ እርምጃ እየወሰደች እንዳለች ተናግረዋል።

ሌሎችም በዩናይትድ ኪንግደም ውሳኔ ደስተኛ ያልሆኑ ከፍተኛ የእስራኤል ባለሥልጣናት በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቻቸው በውሳኔው የተሰማቸውን እያጋሩ ይገኛሉ።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የዩኬ ኃላፊ የሆኑት ሳሻ ዴሽሙኽ በበኩላቸው ዕገዳው “በጣም ዉሱን እና በተለያዩ ክፍተቶች የተሞላ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።

ምዕራባዊያን መንግሥታት ከእስራኤል ጋር የሚያደርጉትን የጦር መሣሪያ ንግድ ተከትሎ ወቀሳ እየደረሰባቸው ሲሆን እስራኤል በሐማስ ላይ በከፈተችው ጦርነት ምክንያት በጋዛ ሰርጥ እየፈፀመችው ባለው ተግባር ትችት ይቀርብባታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በርካታ የሕዝብ እንደራሴዎች፣ የሕግ ሰዎች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ብሪታኒያ ወደ እስራኤል የምትልከውን የጦር መሣሪያ አስመልክቶ ያላቸውን ስጋት አጋርተዋል።

አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለፈው ሐምሌ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ብሪታኒያ ወደ እስራኤል የምትልከውን የጦር መሣሪያ መገምገማቸውን ተናግረዋል።

ላሚ፤ ግምገማው “እስራኤል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋትን ጥሳለች ወይ?” የሚለውን አልተመለከተም ብለው “ይህ ነፃ የመሆን አሊያም የወንጀለኝነት ፍርድ አይደለም” ሲሉ የሀገራቸውን ውሳኔ ተከላክለዋል።

የዩኬ መንግሥት ውሳኔውን ባሰፈረበት ወቅት እስራኤል በጋዛ ያለውን እርዳታ እንዴት ታየዋለች እንዲሁም በቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎች እንዴት ትንከባከባለች የሚለውን ከግምት ማስገባቱን አስታውቋል።

ተንታኞች ውሳኔው ከወታደራዊ አንድምታው ይልቅ ፖለቲካዊው ያመዝናል ይላሉ። እስራኤል 1 በመቶ የጦር መሣሪያ ብቻ ነው ከዩኬ የምታስገባው።

ዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛውን የጦር መሣሪያ ለእስራኤል የምትልክ ሲሆን እስራኤል ከምታስመጣቸው የጦር መሣሪያዎች መካከል 69 በመቶው ከአሜሪካ ነው የሚመጡት።