ጋና ጎረቤቷ የሩሲያ ቅጠረኛ ተዋጊ ቡድንን አስመጥታለች ስትል ለአሜሪካ ክስ አቀረበች

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እና የጋናው ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ-አዶ።

የፎቶው ባለመብት, @SecBlinken

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እና የጋናው ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ-አዶ።
ታትሟል

የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ-አዶ ጎረቤት አገር ቡርኪና ፋሶ ዋግነር የተባለውን ቅጥረኛ የወታደሮች ቡድን ከሩሲያ አስመጥታለች ሲሉ ቅሬታቸውን ለአሜሪካ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ጋር በተገናኙበት ወቅት ነው።

ናና አኩፎ-አዶ ቡርኪና ፋሶ ዋግነር የተሰኘውን ቅጥረኛ ቡድን ከሩሲያ ማስመጣቷ እጅግ አሳሳቢ ነው ሲሉ ለአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ተናግረዋል።

የቅጥረኛ ተዋጊዎች ቡድኑ ዋግነር ቡርኪና ፋሶ መግባቱ የተገለጸው ጋናን ጨምሮ በርካታ የምዕራብ አፍሪካ አገራት በሳህል ቀጠና የጂሃዲስቶች እንቅስቃሴ አሳስቦናል እያሉ ባሉበት ወቅት ነው።  

ናና አኩፎ-አዶ ቅጠረኛ ቡድኑ በጋና ሰሜናዊ የድንበር አቅራቢያ እንደሚገኝ እና እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖችን እንዲዋጋ በቡርኪና ፋሶ ተቀጥሯል ብለዋል።

ቡርኪና ፋሶ በክፍያ መልክ የማዕድን ማውጫ ስፍራ ለቡድኑ ስለመስጠቷ መረጃው አለኝ ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ይህ ዋግነር የሚባለው የቅጥረኛ ወታደሮች ቡድን ከክሬምሊን ትዕዛዝ እየተቀበሉ ግድያ የሚፈጽሙ አልያም የሚዋጉ ናቸው።

ምዕራባዊያን እንደሚሉት ይህ ቡድን ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈጽምና ለንጹሐንም የማይራራ በገንዘብ የሚነዳ ተዋጊ ኃይል ነው።

ዋግነር የቅጥረኛ ተዋጊዎች ቡድን የግል ኩባንያ ሲሆን፣ ወንጀለኞችን ከእስር ቤት ጭምር እየመለመለ በጥሩ ገንዘብ ያዋጋል ይላሉ የምዕራብ ተንታኞች።

ይህን ቡድን የመሠረተውና የሚመራው የቭጌኒ ፕሪጎዚን የተባለ ሰው ነው። ግለሰቡ የቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ረዳት ነበር።

ይህ የዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊዎች ቡድን ከዚህ ቀደም በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በማሊ እና በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በውጊያዎች ላይ ተሳትፏል።

አኩፎ-አዶ በቀጠናው የዴሞክራሲ ጠላቶች ሌት ተቀን እየሰሩ ነው ያሉ ሲሆን በምዕራብ አፍሪካ መፈንቅለ መንግሥት መበራከት አደገኛ ክስተት ነው ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በቡርኪና ፋሶ፣ ሱዳን እና ማሊ የተሳኩ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን በሌሎች አገራት ደግሞ ያልተሳኩ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ተደርገዋል።