በሺዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን የሐማሱ መሪን የአስክሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት ታደሙ

የሃኒያ የአስክሬን ሽኝት ስነ ስርዓት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በኢራን መዲና ቴህራን መኖሪያ ቤት ውስጥ በተፈጸመባቸው ጥቃት ማክሰኞ ሌሊት ሐምሌ 23/ 2016 ዓ.ም. ስምንት ሰዓት ላይ የተገደሉትን የሐማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒያን የአስክሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት ለመታደም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን ተገኙ።

የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ የጸሎት ሥነ ሥርዓቱን የመሩ ሲሆን በመዲናዋ ማዕከል በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የሃኒያን ፎቶ እንዲሁም የፍልስጤምን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ተገኝተው ነበር።

የጸሎቱን ፕሮግራም ተከትሎ የሃኒያን እና የጠባቂያቸውን አስክሬን አጅበው ወደ አዛዲ (ነጻነት) አደባባይ ወስደውታል።

የሽኝት ፕሮግራሙ የተጀመረው የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ ባደረጉት ንግግር ነው።

“ሰማዕቱ ኢስማኤል ሃኒያ በመላው ዓለም የፍልስጤም ሕዝብ ድምጽ ነበር። መሪ ብቻ ሳይሆን በጥበብ የተሞላ ሰው ነበር” ብለዋል።

ኢስማኤል ሃኒያ መቀመጫቸውን ባደረጉባት ኳታር ቀብራቸው ይፈጸማል።

በጋዛ የተኩስ አቁም ድርድር ላይ ትልቅ ሚና የነበራቸው ሃኒያ በቴህራን የኢራን ፕሬዚዳንት ማስዑድ ፔዜሽኪያን በዓለ ሲመት ላይ ከታደሙ ከሰዓታት በኋላ ነው የተገደሉት።

ግድያው የተፈጸመው ሃኒያ ከዚህ ቀደምም ኢራንን በሚጎበኙበት ወቅት በሚያርፉበት ህንጻ ውስጥ መሆኑን የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በወቅቱም ሦስት የሐማስ አመራሮች እና በርካታ ጠባቂዎችም አብረዋቸው በህንጻው ውስጥ እንደነበሩም ገልጸዋል።

የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ኻሊል አል ሃያ፣ ሃኒያ በሚሳኤል በቀጥታ ጥቃት እንደተገደሉ አብረዋቸው የነበሩ እማኞችን ዋቢ አድርገው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የቡድኑ አመራር “በአስደንጋጭ ሁኔታ ውስጥ ወድቋል” ሲሉ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኢራን ግዛት ውስጥ ጥቃት በማድረስ የሐማሱን መሪ ገድላለች ባሏት እስራኤል ላይ አያቶላ አሊ ኻሚኒ ቀጥተኛ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ መስጠታቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የኢራን ባለሥልጣናትን ዋቢ አድርገው ዘግበዋል።

እስራኤል ስለ ግድያው በቀጥታ የሰጠችው አስተያየት የለም።

ይሁን እንጂ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው ባለፉት ቀናት በጠላቶቿ ላይ “የከፉ ጥቃቶችን” አድርሳለች ብለዋል። ጨምረውም በቴህራን ከተፈጸመው ጥቃት በፊት በሊባኖስ የሄዝቦላህ ከፍተኛ አዛዥን መግደላቸውን ተናግረዋል።

ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን ያሳተፈ ጦርነት በቀጣናው ሊጀመር ይችላል የሚለው ስጋት እየጨመረ መጥቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቀጣናው ውጥረቱ በአደገኛ ሁኔታ መባባሱን አስመልክቶ አስጠንቅቀዋል።