ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩኬ ፖሊስ ከሰባ አመት በፊት ‘በስህተት ገድየዋለሁ’ ላለው ሶማሊያዊ ቤተሰብ ይቅርታ ጠየቀ
በዩናይትድ ኪንግደም በግድያ ወንጀል ተከሶ በስህተት የተፈረደበት ሶማሊያዊ አባት ከተገደለ ከሰባ አመት በኋላ ፖሊስ ይቅርታ ጠየቀ። የዩኬና ሶማሊያ ጥምር ዜግነት የነበረው ማህሙድ ማታን የተባለው ግለሰብ ካርዲፍ በሚገኝ የሱቅ ባለቤት የነበረችውን ሊሊ ቮልፖርት ገድሏል በሚልም ነበር በአውሮፓውያኑ 1952 በስቅላት የተገደለው።
ግለሰቡ የቀድሞ ባህር ሰራተኛ ነበር ተብሏል።
የጥፋተኝነት ውሳኔው በአውሮፓውያኑ 1988 ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን በዚህም የወንጀል ጉዳይ ገምጋሚ ኮሚሽኑ ውሳኔውን ሽሮታል ።
የደቡብ ዌልስ ፖሊስ ፍርዱ ጉድለት የተሞላበት መሆኑን አምኖ ይቅርታ ጠይቋል።
"ይህ ፍርድ ከጊዜው ጋር የሚሄድ ነው። ዘረኝነት አድልዎ እና ጭፍን ጥላቻ የወንጀል ፍትህ ስርዓቱን ጨምሮ በመላው ህብረተሰቡ ተስፋፍቶ ነበር" ሲል የፖሊስ ኃላፊ ጄረሚ ቮን ተናግረዋል።
"ማህሙድ ማታን በማይሆን ክስ ምክንያት የፍትህ እጦት ሰለባ እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም፣ ፖሊስም የዚህ አንዱ አካል ነው” ብለዋል።
“ከ70 ዓመታት በፊት በግለሰቡ ላይ ለተፈጸመው በደልና አሰቃቂ ስቃይ ቤተሰቡን እና በዚህ አደጋ ለተጎዱት ሁሉ ለዓመታት ለደረሰው ግፍ ፖሊስን በመወከል ይቅርታ መጠየቁ ትክክል እና ተገቢ ነው።" በማለት አስረድተዋል።
የማህሙድ ማታን ባለቤት ላውራ እና ሶስት ልጆቻቸው ዴቪድ፣ ኦማር እና ኤዲ በመባል የሚታወቀው ሜርቪን ስሙ ከግድያ ወንጀል ነጻ እንዲባል ለ 46 ዓመታት የቆየ ረዥም የዘመቻ ትግል አድርገው ነበር።
ሁሉም ቤተሰቦቹ የሞቱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ፖሊስ ይቅርታ መጠየቁን አስመልክቶ ከስድስት የልጅ ልጆች አንዷ “ቅንነት የጎደለው” ስትል ጠርታዋለች።
“በዚህ በቀጥታ የተጎዱት ሰዎች ከእኛ ጋር ባለመሆናቸው ይቅርታው በጣም ዘግይቷል። በህይወት የሉም እና ከዚህ አመት በኋላ እናዝናለን የሚል ቃል ሰማን” ስትል ታንያ ማታን ተናግራለች።