የአሜሪካ ተቋማት የኮቪድ-19 መነሻን በተመለከተ በተለያየ ጎራ ላይ መቆማቸውን ሪፖርት አመለከተ

ማስክ ያደረጉ ፖሊሶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኮሮናቫይረስ ከቤተ ሙከራ አፈትልኮ የወጣ ነው መባሉን ቻይና በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋለች።
ታትሟል

የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት ኮቪድ -19 ከቻይና ቤተ ሙከራ መነሳቱን የሚያመለክት ቀጥተኛ ማስረጃ አለማግኘታቸውን ይፋዊ ሪፖርት አመለከተ።

የብሔራዊ ደኅንነት ተቋሙ ዳይሬክተር መሥሪያ ቤት እንዳለው ኮቪድ በተፈጥሯዊ መንገድ የተከሰተ ነው የሚለውም ሆነ ከቤተ ሙከራ ያፈተለከ የሚሉት መላምቶች እውነታ ያላቸው ይመስላሉ።

ሆኖም አብዛኞቹ የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት ቫይረሱ በዘረ መል ቅየጣ የተፈጠረ ወይም በላብራቶሪ የተፈበረከ እንዳልሆነ መስማማታቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

የወረርሽኙ መነሻ በአሜሪካ ጠንካራ ክርክሮችን ሲያስነሳ ቢቆይም አሁንም ይህ ነው የሚባል ድምዳሜ ላይ አልተደረሰም።

ቻይናም ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ያፈተለከ ነው መባሉን በተደጋጋሚ ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።

የደኅንነት ተቋሙ ዳይሬክተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት አርብ ምሽት ላይ ይፋ የተደረገውም፣መጋቢት ወር ላይ ኮንግረንሱ የአሜሪካ የደኅንነት ተቋም በቻይና ውሃን ስለሚገኘው የቫይረስ የጥናት ተቋም የሚያውቀውን እንዲያስረዳ 90 ቀናት እንዲሰጠው ውሳኔ ካሳለፈ ከወራት በኋላ ነው።

ባለ 10 ገጽ ሪፖርቱ እንደገለጸው፣የማዕከላዊ ደኅንነት ተቋሙ (ሲአይኤ) እና ሌላ ተቋም የኮቪድ-19 ወረርሽኙን ትክክለኛ መነሻ ማወቅ አልቻሉም።ምክንያቱ ደግሞ መነሻው ተፈጥሯዊ አሊያም ቤተ ሙከራ በሚል የቀረቡት መላምቶች አሳማኝ በሆኑ ግምቶች ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው እና ይህንን በሚመለከትም እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ ሪፖርቶች በማጋጠማቸው ነው።

በዚህም አራቱ የደኅንነት ተቋማት ቫይረሱ ከእንስሳት ወደ ሰው የተላለፈ መሆኑን ማመናቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፣የኢነርጂ መሥሪያ ቤቱ እና የአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ (ኤፍቢአይ) ደግሞ ቫይረሱ ከቻይና ቤተ ሙከራ የወጣ ነው በሚለው እምነታቸው ቀጥለዋል ብሏል።

ሆኖም የአሜሪካ የደኅንነት ማኅበረሰብ እስካሁን ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ሊያፈተልክ የሚችልበትን እድል ውድቅ ማድረግ እንዳልቻሉ የሪፖርቱ ግኝት ጠቅሷል።

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ሁሉም የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት ኮቪድ-19 ባዮሎጂካል ጦር መሳሪያ ሆኖ እንዳልበለጸገ ግን ተስማምተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሪፖርቱ ጨምሮም የውሃን የቫይረስ ጥናት ተቋም እና የቻይና ጦር የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሊያስከትል በሚችል ቫይረስ ላይ ባይሆንም ለማኅበረሰብ ጤና ምርምር በኮሮናቫይረስ ላይ በትብብር እየሰሩ ነበር ብሏል።

ተመራማሪዎቹም ‘ቺሜራስ’ ወይም የኮሮናቫይረሶች ቅይጥ ሲሰሩ እንደነበርና ሆን ተብለው የተደረጉ ለውጦችን ሊደብቁ የሚችሉ የዘረ መል መለወጫ ዘዴዎችን ሲጠቀሙ እንደነበር ጠቅሷል።

የተወሰኑ ተመራማሪዎች ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት በቂ የሆነ ጥንቃቄ ሳያደርጉ ቀርተው ሊሆን እንደሚችልም ገልጿል።

ነገር ግን በውሃን ቤተ ሙከራ ጥንቃቄ ላይ ስለተከሰተው አጋጣሚ የአሜሪካ ደኅንነት አያውቅም ብሏል ሪፖርቱ።

በ2019 በክረምትና በበጋ ወራት መካከል ባለው ወቅት እዚያ ያሉ በርካታ ተመራማሪዎች ታመው እንደነበር የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ነገር ግን ህመማቸው በተለያዩ በሽታዎች ሳቢያ የተከሰተ ሊሆን ይችላል ብሏል። ተመራማሪዎቹ ያሳዩት የነበረው የተወሰኑት ምልክቶችም ከኮቪድ 19 ጋር የሚመሳሰሉ አልነበሩም ብሏል።

ሪፖርቱን አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት በዶናልድ ትራምፕ አስተዳዳር ዘመን የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉት ጆን ራትክሊፍ በበኩላቸው “ግራ ማጋባታቸውን ቀጥለዋል” ሲሉ ፕሬዚደንት ባይደንን ከሰዋል።

ራክሊፍ በመግለጫቸው “ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ማምለጡ በሳይንስ፣ በእውቀት እና በምክንያታዊ አስተሳሰብ የተደገፈ ብቸኛው ጽንሰ ሃሳብ ነው” ብለዋል።

ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ አፈትልኳል የሚለውን ሃሳብ የሚደግፉትም፣ በውሃን የሚገኘው የቫይረስ ጥናት ተቋም በ2019 መጨረሻ ላይ የኮቪድ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት የውሃን የባህር ምግብ ገበያ 40 ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በ2021 በቻይና እና በዓለም ጤና ደርጅት በጋራ የተሰራው ምርመራም ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ አፈትልኳል መባሉ “ በፍጹም ሊሆን የማይችል ነው ” ብሏል።

ሪፖርቱ በበርካታ ባለሙያዎች ዘንድ ጥያቄን የፈጠረ ሲሆን ድርጅቱም ጠንካራ ትችቶችን አስተናግዷል።

አንዳንድ ባለሙያዎች ወደ ሰባት ሚሊየን የሚጠጋ የዓለም ሕዝብን የቀጠፈው የኮቪድ 19 ትክክለኛ መነሻ ጭራሽኑ ላይታወቅ ይችላል ብለዋል።