ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሺንዞ አቤ ግድያ ወቅት የጥበቃ ክፍተት እንደነበረ የጃፓን ፖሊስ አመነ
የጃፓን ፖሊስ ባለፈው ዓርብ በደቡባዊቷ ናራ ከተማ የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ግድያ በተፈጸመበት ወቅት የፀጥታ ጥበቃ ክፍተቶች እንደነበሩ አመነ።
የናራ ፖሊስ አዛዥ ቶሞአኪ ኦኒዙካ "በፀጥታ አጠባበቁ ላይ ችግሮች እንደነበሩ መካድ አይቻልም" ብለዋል።
ሟቹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ለጃፓን የላይኛው ምክር ቤት የሚወዳደር ዕጩን ወክለው ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸው ማለፉ ጃፓናን ብሎም በመላው ዓለም ድንጋጤን ፈጥሯል።
ሺንዞ አቤ ቅስቀሳ ሲያደርጉበት የነበረው የምክር ቤት ምርጫ ቀድሞ በታቀደው መሠረት ዕሁድ ዕለት ተካሂዷል።
የምርጫው ትንበያ እንደሚያሳየው ሺንዞ አቤ ሲቀሰቅሱለት የነበረው እና ከፍተኛ ተደማጭነት ያለው የገዢው ሊየበራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኤልዲፒ) እንዲሁም ጥምር አጋሩ ኮሜይቶ አብላጫውን ድምጽ ያገኛሉ ተብሎ ይገመታል።
በአቤ ላይ ግድያውን በመፈጸም የተጠረጠረው የ41 ዓመቱ ቴሱያ ያማጋሚ አንድ በስም ያልተጠቀሰ ተቋም ላይ ቂም ይዞ ነበር ሲል ፖሊስ ይፋ አድርጓል።
የጃፓን መገናኛ ብዙኃን ለምርመራው ቅርብ የሆኑ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገቡት ከሆነ ተጠርጣሪው ወላጅ እናቱን የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ከከተተ አንድ የሃይማኖት ቡድን ጋር ሺንዞ አቤ ግንኙነት እንዳላቸው ብሎ ያምናል።
ፖሊስ አክሎም ተጠርጣሪው በቤት ውስጥ በተሰራ ሽጉጥ ተጠቅሞ ወደ ሺንዞ አቤ ላይ መተኮሱን ማመኑን ተናግሯል።
"ለእኛ አስቸኳዩ ጉዳይ ምን እንደተፈጠረ ለማብራራት ጥልቅ ምርመራ ማካሄድ ነው" ያሉት የፖሊስ አዛዡ ኦኒዙካ፤ ተፈጥረዋል ያሏቸውን ክፍተቶች የት ላይ እንደሆኑ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ተጠርጣሪው ያማጋሚ በጃፓን የባሕር ኃይል ውስጥ ለሦስት ዓመታት ማገልገሉን ለፖሊስ መናገሩም ተገልጿል። በቅርቡ ደግሞ በምዕራብ ጃፓን በሚገኝ ፋብሪካ ውስጥ ሲሰራ ነበረ ተብሏል።
አቤ ሕይወታቸው ያለፈበት ጥቃት የተፈጸመባቸው ከዋና ከተማዋ ቶኪዮ በስተደቡብ 480 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ናራ ከተማ ውስጥ በሚካሄድ የምክር ቤት ምርጫ ቅስቀሳ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ነበር።
አቤ በጥይት ከተመቱ በኋላ ወዲያውኑ መሬት ላይ የወደቁ ሲሆን፣ በፍጥነት ወደ ህክምና ቢወሰዱም ሕይወታቸውን ማትረፍ አልተቻለም።