ሩሲያ እስር ቤት ሞቶ የተገኘውን የፑቲን ተቃዋሚ አስክሬን ‘ደብቃለች’ ሲሉ የሟች ባልደረቦች ገለጹ

ታትሟል

ባለፈው ሳምንት በሩሲያ አርክቲክ እስር ቤት ውስጥ ሕይወቱ ያለፈውን የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ አሌክሲ ናቫልኒን አስክሬን ማግኘት እንዳልቻሉ ባልደረቦቹ ተናገሩ።

ከባልደረቦቹ አንዱ የሆነችው ኪራ ያርማይሽ የፖለቲከኛው ወላጅ እናት ሉሜላ የልጃቸው አስክሬን የሚሰጣቸው እየተደረገ ያለው የአስክሬን ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ እንደሆነ እንደተነገራቸው ገልጻለች።

የናቫንሊ የሥራ ባልደረቦች ሙስናን በመታገል የሚታወቀው ፖለቲከኛ እስር ቤት ሳለ በፕሬዝዳንት ፑቲን ትዕዛዝ እንደተገደለ ያምናሉ።

አንድ የመብት ተሟጋች ድርጀት ለፖለቲከኛው ሐዘናቸውን እና ያላቸውን አክብሮት በአደባባይ የገለጹ ፖለቲከኞች መታሰራቸውን ገልጿል።

የምዕራባውያን መንግሥታት ለፖለቲከኛው ድንገተኛ ሞት ተጠያቂዎቹ የሩሲያ ባለሥልጣናት ናቸው ብለዋል። የበለጸጉት የቡድን 7 አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደግሞ የአሟሟቱን መንስዔ በአፋጣኝ ግልጽ እንድታደርግ ሩሲያን ጠይቀዋል።

የ47 ዓመቱ ፖለቲከኛ ህመም ካጋጠመው በኋላ ሕይወቱ ማለፉን የሩሲያ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ከገለጸ በኋላ ፕሬዝዳንት ፑቲን በግልጽ ያሉት ነገር የለም።

ከክስተቱ በኋላ የፑቲን ጽህፈት ቤት የሆነው ክሬምሊን ስለጉዳዩ እንዳወቀ እና ፕሬዝዳንቱም መረጃው እንደተነገራቸው ገልጿል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲከኛውን ሞት መንስኤ በተመለከተ “ወደ አንድ ወገን ያደላ እና ተጨባጭ ያልሆነ” አስተያየቶችን ውድቅ አድርጓል።

ናቫልኒ በሩሲያ የፑቲንን አስተዳደር በመቃወም ከሚታወቁ ፖለቲከኞች አንዱ የነበሩ ሲሆን፣ በፖለቲካዊ ክስ ምክንያት 30 ዓመታት ተፈርዶበት ከሞስኮ 1900 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ እያሳለፈ ነበር።

የሩሲያ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በቅርቡ ልጃቸው እየተራመደ ሳለ ድንገት ወድቆ ሕይወቱ ማለፉን ለእናቱ እንደተነገሯቸው የሥራ ባልደረቦቹ ገልጸዋል።

ሌላኛው የፖለቲከኛው የስራ አጋር የሆነው አይቫን ዛዶንቭ ሟች ባልታወቀ ምክንያት በሚመጣ የልብ ስራ ማቆም ገጥሞት ህይወቱ እንዳለፈ እናቱ መናገራቸውን ገልጿል።

የስራ ባልደረቦቹ እንደሚገልጹት ከሆነ የፖለቲከኛው አስክሬን ታስሮ ይገኝበት ከነበረው እስር ቤት አቅራቢያ ወደሚገኝ ከተማ መወሰዱን ለእናቱ ቢነገራቸውም አለ የተባለበት ቦታ ሲደርሱ ዝግ ሆኖ አግኝተውታል።

የእስር ቤቱ ባለስልጣናት ለእናቱ አስክሬኑ ላይ በተደረገ የመጀመሪያ ምርመራ ድምዳሜ ላይ መድረስ አለመቻሉ እና ሁለተኛ ምርመራ እንደሚከናወን እንደተገለጸላቸውም ተነግሯል።

ታዲያ የፖለቲከኛው የስራ አጋሮች የሩስያ መንግሥት ሆን ብሎ አስክሬኑን በመያዝ ማስረጃዎች እያጠፋ እንደሆነ ከሰው አስክሬኑ በፍጥነት ለቤተሰቦቹ እንዲመለስ አሳስበዋል።

በሌላ ዜና በመላው ሩስያ ለሟች ፖለቲከኛው ያላቸውን ክብር እና ሀዘን በአደባባይ የገለጹ ከ400 በላይ ሰዎች በመላው ሩስያ መታሰራቸውን በሩስያ ላይ የሚያተኩር ገለልተኛ የስብአዊ መብት ጉዳዮች ታዛቢ ተቋም ገልጿል።

ተቋሙ እነዚህ ሰዎች በ36 የሩስያ ከተሞች መታሰራቸው ገልጾ በርካታውን ቁጥር የሚይዙት ከሴንት ፒተርስበርግ ከተማ የታሰሩት እንደሆነ ጠቋሟል።

ባለፈው ቅዳሜ በሞስኮ ለሟቹ ሻማ በማብራት እና አበባ በማስቀመጥ ሀዘናቸውን የገለጹ ሰዎች በፖሊስ መታሰራቸው ተሰምቷል።