ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩክሬን በከፍተኛ ሁኔታ ስትከላከላቸው የነበሩ ግዛቶችን እያጣች መሆኑን ወታደሮቿ ተናገሩ
ዴኒስ ያሮስላቭስኪ በከፍተኛ ብስጭት ውስጥ ነው።
ዴኒስ በአውሮፓውያኑ 2020 የሩሲያ ጦር የመጀመሪያ ዙር ወረራ በኻርኪቭ ክልል በኩል የዩክሬን የልዩ ወታደራዊ አደረጃጀት አዛዥ ሆኖ ተዋግቶ ሩሲያውያንን መልሷል።
ነገር ግን ከሁለት ዓመት በኋላ ዴኒስ እና ጓዶቹ አሁን ያንን ዘመቻ ድጋሚ ለማድረግ መገደዳቸው አልቀረም።
በኻርኪቭ ክልል በኩል የሩሲያ ወታደሮች በቅርቡ ትልቅ ባይባልም ነገር ግን ስትራቴጅካዊ ድልን ተቀዳጅተዋል። ቢያንስ 100 ኪሎ ሜትር የዩክሬን ድንበርን ዘልቀው ገብተዋል።
ዴኒስ የዩክሬን መከላከል ምን እክል እንደገጠመው ለማወቅ እየጣረ ነው። “የመጀመሪያ የመከላከያ መስመር አልነበረም። አይተነዋል።
ሩሲያውያን በቀላሉ ነው የገቡት። ምንም የፈንጅ አጥር ያልተደረገበት ክልልን ነው አልፈው የገቡት” ። ብሏል ዴኒስ። ሩሲያውያን በቀላሉ ድንበሩን ጥሰው ሲገቡ የሚያሳይ የድሮን ምስል ለቢቢሲ አጋርቷል።
ባለስልጣናት የመከላከያ መስመሩ በከፍተኛ ወጭ ተሰርቶ እንደነበር ይናገራሉ።
ነገር ግን ያ ተሠራ የተባለው የመከላከያ መስመር እዚያ እንዳልነበር ዴኒስ አረጋግጧል። “ይህ ወይ ግዴለሽነት ነው፣ አለበለዚያ ደግሞ ሙስና ነው። ከአቅም በላይ ሆኖ ሳይሆን ክህደት ተፈጽሞብን ነው” በማለት ሁኔታውን ያብራራል።
ይህ ሊሆን እንደሚችል ሁሉም ያውቅ ነበር። ሩሲያ በድንበሩ አካባቢ ጦር እያከማቸች እንደነበር ዩክሬናውያንም ምዕራባውያንም የመረጃ ሰዎች ጠንቅቀው ያውቁ ነበር።
እስከ 30 ሺህ የሚገመት ጦር እያከማቹ ነበር።
ፕሬዝዳንት ፑቲንም ሩሲያን ለመጠበቅ በኻርኪቭ ክልል ውስጥ የመከላከያ አጥር እንደሚያበጁ በይፋ ገልጸው ነበር።
በዩክሬን በኩል ደግሞ ደካማ ዝግጅት ነበረ። ዴኒስ ከሩሲያ ድንበር አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ቮቭቻንስክ ከተማ ለማምራት ተሰናድቷል።
ነገር ግን ከተማዋን የሩሲያ ወታደሮች እንደተቆጣጠሯት እየተነገረ ነው። ዴኒስም ስጋቱን ገልጿል።
ከጦርነቱ በፊት በከተማዋ 20 ሺህ ሰዎች ይኖሩባት ነበር። ነገር ግን ጦርነቱ ሲጀመር አብዛኛዎቹ ተሰደው አሁን በከተማዋ የሚገኙት ነዋሪዎች ከ3 ሺህ በታች ናቸው።
በኻርኪቭ ክልል ሩሲያ ወረራዋን ለማስፋት ሁሉንም አማራጮች ተጠቅማለች። ኦሌስኪ የተባለ የከተማው ፖሊስ እንደሚገልጸው ሰዎች አሁን በብዛት ከተማዋን ለቀው እየወጡ ነው።
ምክንያቱም የሩሲያ የማያቋርጥ የከባድ መሣሪያ ጥቃት በማየሉ ነው። ኦሌስኪ እንደሚለው በሰዓት ቢያንስ ከ50 እስከ 60 ከባድ መሣሪያ ወደ ከተማዋ ይተኮሳል።
በአብዛኛው ከተማዋ ውስጥ የሚቆዩት አቅመ ደካሞች እና ዝቅተኛ ነዋሪዎች ናቸው። እንዲያም ሆኖ አንዳንድ ዕድሜ ጠገብ ሰዎች እየተሰደዱ ነው።
የ65 ዓመት አዛውንቱ ኦሌክሳንደር ከተማዋን ለቀው ከሚሰደዱ አዛውንቶች መካከል አንዱ ናቸው። ሁለት አነስተኛ ሻንጣዎችን ይዘው የፖሊስ መኪና ላይ ተሳፍረዋል።
ዓላማቸው ወደ ጀርመን መሻገር ነው። እንዴት መጓዝ እንዳለባቸው ግን የሚያውቁት ነገር የለም።
በሰሜን በኩል አዲስ ግንባር መፈጠሩ የዩክሬንን ውስን ሃብት ለማብቃቃት ተጨማሪ ችግር ፈጥሯል። አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ ለመወሰን ጊዜ መውሰዷ የዩክሬን ወታደሮች በተተኳሽ እጥረት እንዲቸገሩ አድርጓል።
በአማካይ ዩክሬን ለሩሲያ 10 ከባድ መሣሪያ ተኩስ አጸፋ የምትሰጠው አንድ ብቻ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ዩክሬን በራሷም የመከላከያ መስመሮችን በመዘርጋት እና ግብዓትን በፍጥነት በማጓጓዝ ረገድ ትልቅ ችግር እንዳለባት የኻርኪቭ ሽንፈቷ አንዱ ማሳያ ነው።
በእርግጥ የኻርኪቭ ከተማ አሁንም ከስጋት ነጻ መሆኗን የዩክሬን ባለስልጣናት እየተናገሩ ነው።
ነገር ግን የሩሲያ ወታደሮች ግስጋሴያቸው እስካልተገታ ድረስ በቅርቡ በከባድ መሣሪያ ከበባ ውስጥ የመግባት ዕድሏ እየሰፋ ይመጣል።
ዴኒስ እንደሚለው ሩሲያ ሙሉ ትኩረቷን ወደ ምስራቅ በማድረግ ዶንባስን ሙሉ በሙሉ ለመጠቅላል ታቅዳለች።
ከዚያም በተጨማሪ ለአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በተዘረጋው የጦር ግንባር፣ ሩሲያ የዩክሬንን ደካማ ይዞታዎች እያጠናች ልታጠቃ ትችላለች ብሏል።
“በእርግጥ በጣም ተበሳጭቻለሁ” የሚለው ዴኒስ፣ “በ2022 ይህንን አካባቢ ለመከላከል ስንዋጋ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሰውተናል። በሕይወታችን ተወራርደናል። አሁን ደግሞ የሆነ አካል የመከላከያ መስመር ባለመዘርጋቱ በድጋሚ ሰዎችን እየገበርን ነው” በማለት ሁኔታውን ገልጿል።