በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የቀድሞዋ የስኮትላንድ መሪ ተለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የቀድሞ የስኮትላንድ ተቀዳሚ ሚኒስትር ኒኮላ ስተርጅን ያለተጨማሪ የምርመራ ቀጠሮ እና ክስ ከእስር ተለቀዋል።
የቀድሞ ተቀዳሚ ሚኒስትሯ ስኮቲሽ ናሽናል ፓርቲ ወይም ኤስኤንፒ ፋይናንስ ላይ እየተደረገ ካለው ምርመራ ጋር በተያያዘ ነበር ትላንት የታሰሩት።
ኒኮላ ስተርጅን በፖሊስ መርማሪዎች ጥያቄ ከቀረበባቸው በኋላ ነው ከእስር የተፈቱት።
ከእስር ከተፈቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት “ምንም አይነት ያልተገባ ድርጊት እንዳልፈጸምኩኝ አውቃለሁ” ብለዋል።
ፖሊስ ከእስር መፈታታችውን በተመለከተ ለዘውድ ምክር ቤት እና ለዐቃቤ ሕግ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ገልጿል።
ፖሊስ ላለፉት ሁለት ዓመታት ለስኮትላንድ ሕዝበ ውሳኔ ዘመቻ የሚውል ከገለልተኛ አካላት ለስኮቲሽ ናሽናል ፓርቲ ወይም ኤስኤንፒ የተመደበው 660 ሺህ ፓውንድ የገባበትን ለማወቅ ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል።
የፖሊስ መኮንኖች ስተርጅን ከእስር ከመልቀቃቸው በፊት እሳቸውን ለመልቀቅ ወይም ክስ ለመመስረት በተመለከተ ውሳኔ ላይ ለመድረስ እስከ 12 ሰዓታት የፈጀ ምርመራ አድርገዋል። ከዚያም ያለክስ እና ተጨማሪ ምርመራ አሰናብተዋቸዋል።
ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገበት ያለ ሰው ከእስር ቢለቀቅም ዳግም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሊውል ይችላል።
ስተርጅን ከእስር መለቃቸውን ፖሊስ ባረጋገጠ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በትዊተር ገጻቸው ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ምንም እንዳላጠፋሁ እርግጠኛ ሆኜ ራሴን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳገኘው በጣም አስደንጋጭ እና አሳዛኝ ነው” ያሉት የቀድሞዋ ከፍተኛ ባለሥልጣን “አሁን ኤስኤንፒ እየተደረገ ያለው ምርመራ ለሰዎች አስቸጋሪ እንደ ሆነ አውቃለሁ። ብዙዎች እኔ ላይ እምነት ስላሳዩ አመሰግናለሁ። እኔ ኤስኤንፒንም ሆነ አገሬን የሚጎዳ ምንም ነገር አልፈጸምኩም” ብለዋል።
የስኮትላንድ ተቀዳሚ ሚኒስትር እና የኤስኤንፒ መሪ የነበሩት ስተርጅን ባለፈው የካቲት ነበር ሀምዛ የሱፍ በተባሉ ፖለቲከኛ የተተኩት።
የቀድሞዋ ሚኒስትር ቀድሞ የእምነት ክህደት ቃላቸው ከሰጡ በኋላ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ተደርጎባቸዋል።
ስተርጅን ከመታሰራቸው ወራት ቀደም ብሎ የኤስኤንፒ መሪ የነበሩት ባለቤታቸው ፒተር ሙሬል በቁጥጥር ስር ውለው ነበር። ባለቤታቸው በተሳሩበት ተመሳሳይ ቀን ቤታቸው በፖሊስ ብርበራ ተደርጎበታል።












