በደቡብ አፍሪካ በቤተሰብ ጥል መካከል የዙሉ ንጉስ ተሰየሙ

ሚሱዙላ ካ ዝዌሌቲኒ

የፎቶው ባለመብት, KwaZulu-Natal Government

ታትሟል

ለአንድ ዓመት በዘለቀው የቤተሰብ ጥል መካከል ሚሱዙላ ካ ዝዌሌቲኒ በደቡብ አፍሪካ በህላዊ ስነ ስርዓት መሰረት የዙሉ ንጉስ ሆነው ተሰየሙ።

የ48 አመቱ ሚሱዙላ የቀደመው የዙሉ ንጉስ ልጅ ሲሆኑ ነገር ግን አንዳንድ የንጉሳዊ ቤተሰብ አባላት ትክክለኛ ወራሽ እንዳልሆኑና የሟቹን ንጉስ ኑዛዜም አጭበርብረዋል በማለት ሲከራከሩ ቆይተዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቅዳሜው ባህላዊ የዘውድ ሥነ ሥርዓት ለመታደም በክዋካንገላማንንጋኔ ቤተ መንግሥት ተሰብስበው ነበር።

ሚሱዙላ የዙሉ ንጉስ ሆነው እንደተሰየሙ ለህያዋንም ሆነ ለሙታን ከመነገሩ በፊት ቅድመ አያቶቻቸውን ለመለመን ወደ ተቀደሰው የከብት ማደሪያ ገብተዋል።

ለስርዓተ ሲመቱ ያደኑትን የአንበሳ ቆዳ እንዲለብሱ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህም በዋናነት የተመረጡ ሰው መሆናቸውን ለማረጋገጥ ቁልፍ ስርዓት ነው።

ለበዓሉ ዝግጅት ከ10 በላይ ላሞች ታርደዋል።

በሚቀጥለው ወርም ብሄራዊ የሆነው ሥነ-ሥርዓት በመንግሥት አስተናጋጅነት የሚዘጋጅ ሲሆን ንጉሱም ይገኛሉ።

ዙፋኑ ምንም አይነት መደበኛ የፖለቲካ ስልጣን ባይኖረውም ነገር ግን ከደቡብ አፍሪካ አንድ አምስተኛው ህዝብ ዙሉ ሲሆን ለንጉሳዊ አገዛዙ በዓመት ከ4.9 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት በግብር መልኩ ይደግፉታል። ንጉሳዊ አገዛዙም ትልቅ ተፅእኖ ያለው ነው።

የዙሉ መንግሥት አኩሪ ታሪክ ያለው ሲሆን በአውሮፓውያኑ 1879 የኢሳንድልዋና ጦርነት የብሪታንያ ወታደሮችን በማሸነፍ በዓለም ታሪክ ስምን ተጎናጽፏል።

በንጉሳዊ አገዛዝ ተተኪ ማን ይሆን የሚለው ከፍተኛ ፉክክር የሚታይባቸው ሲሆን እና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ደም አፋሳሽ ናቸው።

ስመ ጥሩው ንጉስ ሻካ ካ ሴንዛንዛንኮና ዙፋኑን ለመንጠቅ ወንድማቸውን በአውሮፓያኑ 1816 የገደላቸው ሲሆን ከዛም ከዓመታት በኋላ በእህታቸው ልጅ በተቀነባበረ ሴራ ራሳቸውም ተገደሉ።

ነገር ግን የንጉስ ጉድዊል ዝዌሊቲኒ ካ ብሄኩዙሉ ሞትን ተከትሎ የመጡት ክስተተቶች አሳፋሪ የህዝብ ትዕይንት ተብለዋል።

የተለያዩ የንጉሣዊ ቤተሰብ አንጃዎችም እጩዎቻቸውን በመያዝ ወደ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ወስደውት ነበር።

ባለፈው አመት ህይወታቸው ያለፈው ንጉስ ዝዌሊቲኒ ስድስት ሚስቶች የነበሯቸው ሲሆን ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ገዝተዋል።