ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሕንድ አውሮፕላን ላይ ከተፈጸመ የሽብር ጥቃት ነጻ የተባለው ግለሰብ ካናዳ ውስጥ ተገደለ
እአአ 1985 ላይ በኤይር ኢንዲያ የበረራ ቁጥር 182 ላይ በተፈጸመው ጥቃት ምክንያት ምርመራ ተደርጎበት ነጻ የተባለው ግለሰብ ካናዳ ውስጥ በጥይት ተመትቶ ተገደለ።
የካናዳ ፖሊስ እንዳስታወቀው ሪፑዳማን ሲንግሃ ማሊክ፣ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ውስጥ ነው የተገደለው።
ግለሰቡ መኪናው ውስጥ ሳለ በጥይት ተመትቶ ከመገደሉን በተጨማሪ ወንጀሉ በተፈጸመበት አካባቢ የተቃጠለ መኪና ማግኘቱን ፖሊስ አሳውቋል።
ማሊክ እአአ 1985 በተፈጸመው እና 329 ሰዎችን በገደለው ጥቃት ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ የለኝም ሲል ቆይቷል።
ማሊክ እአአ 2005 ላይ ከተጠርጠረበት ወንጀል ነጻ ቢባልም፤ ፖሊስ የዚህን የሽብር ጥቃት አቀነባባሪዎችን አድኖ መያዝ አልቻለም ተብሎ አሁን ድረስ ይተቻል።
ይህ በሕንድ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት መቀመጫቸውን ካናዳ ባደረጉ የሲክ እምነት ተከታዮች ሳይፈጸም እንደማይቀር ይገመታል።
ይህም ጥቃት በሲክ ግዛት ቅዱስ ተብሎ በሚጠራው ‘ጎልደን ቴምፕል’ ላይ ሕንድ በእአአ 1984 ላካሄደችው ዘመቻ የበቀል እርምጃ ተደርጎ ይታሰባል።
ይህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት በካናዳ ታሪክ በርካቶችን ለሞት የዳረገ የሽብር ተግባር ነው ተብሎ ተመዝግቧል።
ከጥቃቱ በኋላ ነጋዴ የሆነው ማሊክ እና አብሮት በወንጀሉ ተጠርጥሮ የተከሰሰው አጃኢብ ሲንግሃ ባግሪ ተመስርቶባቸው ከነበረው የጀምላ ግድያ እና የቦምብ ጥቃት የመፈጸም ሴራ ወንጀሎች ነጻ ተብለዋል።
ማሊክ እና አብሮት ተጠርጥሮ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው ባግሪ፤ የፈንዳው አውሮፕላን ላይ ቦምብ ጠምደዋል ተብለው ይከሰሳሉ።
የካናዳ ፖሊስ ማሊክ ለምን ዒላማ ተደረገ የሚለውን ለመለየት ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ከካናዳ ተስቶ ወደ ሕንድ በረራ እያደረገ የነበረው ኤይር ኢንዲያ የበረራ ቁጥር 182 አውሮፕላን አየርላንድ ሰማይ ላይ ከፈንዳ በኋላ አሳፍሯቸው የነበሩት 329 ሰዎች በሙሉ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ከተሳፋሪዎቹ መካከል አብዛኛዎቹ ቤተሰብ ጥያቃ ከካናዳ ወደ ሕንድ ሲጓዙ የነበሩ ካናዳውያን ዜግነት የነበራቸው ሰዎች ናቸው።