ታዋቂው አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይ ብሩስ ዊልስ በ‘ዲሜንሺያ’ መያዙን ቤተሰቦቹ ገለፁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ብሩስ ዊልስ ዲሜንሺያ የተባለ የጤና ችግር እንደገጠመው ቤተሰቦቹ ይፋ አደረጉ።
ቤተሰቦቹ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት መግለጫ “በመጨረሻም ግልጽ የሆነ ምርመራ መኖሩ እፎይታ ሰጥቶናል” ብለዋል።
ብሩስ ዊልስ ያጋጠመው ይህ ዲሜንሺያ የተባለው የጤና ችግር አይነት እንቅስቃሴን እና ሌሎች ተፈጥሯዊ ሂደቶችን መቆጣጠርን አዳጋች የሚያደርግ ነው።
የ67 ዓመቱ ተዋናይ ባለፈው ዓመት አፋሲያ (aphasia) በተባለ ለንግግር እክል የሚያጋልጥ ህመም መያዙ ይፋ ተደርጎ ነበር።
ቤተሰቡ በመግለጫቸው ላይ አድናቂዎቹ ያልተገደበ ፍቅራቸውን ስለገለጹ ከልብ የመነጨ ምስጋና አቅርበዋል።
አክለውም ፍሮንቶቴምፖራል ዲሜንሺያ (frontotemporal dementia) የተባለው እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ላይ የሚከሰት ህመም መሆኑን ገልጸዋል።
“ዛሬ ለዚህ በሽታ ምንም ዓይነት ሕክምና የለም። ወደ ፊት ይህ እውነታ ይቀየራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብሏል የቤተሰቡ መግለጫ።
ብሩስ ዊልስ ስሙ የገነነው እኤአ በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ በዳይ ሀርድ፣ ዘ ሲክስ ሴንስስ፣ አርማጌዶን እና ፐልፕ ፊክሽን ፊልሞች ላይ ከተወነ በኋላ ነው።
ብሩስ ዊልስ ለአምስት ጎልደን ግሎብ ሽልማቶች ላይ ታጭቶ በአንዱ ማሸነፍ ችሏል።
በተጨማሪም ሦስት ለኤሚ ሽልማትም ታጭቶ ሁለቱን ማሸነፍ ችሏል።
ባለፈው ዓመት አፋሲያ በተባለ በሽታ መታመሙን ቤተሰቡ ይፋ ካደረገ በኋላ ከትወና ዓለም መራቁን ተናግረው ነበር።
የአእምሮ ጤና እንክብካቤ እና ምርምሮች ላይ በመስራት የምትታወቀው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ማርሪ ሽሪቨር፣ ይህንን ዜና ከሰማች በኋላ በትዊተር ሰሌዳዋ ላይ “ለብሩስ ዊልስ እና ቤተሰቦቹ የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘኔን መግለጽ እፈልጋለሁ። በተጨማሪም ስለዚህ የበለጠ ትኩረትን ስለሚሻው ህመም በይፋ በመናገራቸውም ያለኝን አድናቆት እገልጻለሁ” ብላለች።
“ሰዎች ወደፊት በመጡ ቁጥር ሁላችንንም ያግዘናል። ሰዎች ተመርምረው ውጤታቸውን ባወቁ ጊዜ እጅጉን ፈታኝ ይሆናል፤ ነገር ግን ለበርካቶች ተመርምሮ ማወቅ እፎይታ አለው።”
ብሬኪንግ ባድ በተሰኘው የቴሌቪዥን ድራማ ላይ የተወነው አሮን ፖል በበኩሉ ዊልስ “ታላቅ ሰው ነው” ካለ በኋላ “ውድ ጓደኛዬ እወድሃለሁ” ሲል አክሏል።
አሜሪካዊቷ ድምጻዊ እና ተዋናይ ኩዊን ላቲፋ በኢንስታግራም ገጿ ላይ “እግዚአብሔር ይባርክህ ውድ ወንድሜ፤ እንወድሃለን!!! መልካሙን ሁሉ እመኝልሀለው። አንተን እና ቤተሰቦችህን ስላበረከታችሁልን መዝናኛ አመሰግናለሁ” ብላለች።
እንደ ዩናይትድ ኪንግደም የጤና መሥሪያ ቤት ድረ ገጽ መረጃ ከሆነ ይህ ህመም “ያልተለመደ ዓይነት” እና የባሕርይ እና የቋንቋ ችግር የሚፈጥር ነው።
ህመሙ የእንቅስቃሴ ተግዳሮት፣ የሽንት እና ሰገራ መቆጣጠር ችግር የሚያስከትል ሲሆን፣ በሂደትም የጡንቻ መስነፍ ይከተላል።












