የደኅንነት ችግር እና የምግብ እጥረት የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ አጀንዳዎች እንደሚሆኑ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአፍሪካ እየተባባሰ የመጠው የደኅንነት እጦት ችግር እንዲሁም የምግብ እጥረት ቀውስ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ዋነኛ አጀንዳዎች እንደሚሆኑ ተገለጸ።
የአፍሪካ ኅብረት የሚኒስትሮች ጉባኤ ቀድሞ የተጀመረ ሲሆን፣ የመሪዎች ጉባኤ ደግሞ ከነገ ቅዳሜ እና እሁድ የካቲት 11 እና 12/2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ሁለት ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው በዚህ ጉባዔ ላይ በአህጉሪቱ ያለውን የደኅንነት ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችል ገንዘብ ከአሜሪካ፣ ከአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት እና ከአውሮፓ ኅብረት ለማሰባሰብ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ይደረጋል።
የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ደኅንነት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶዬ አዲሱን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘት ለዕቅዱ ድጋፍ ያሰባስባሉ ብሏል ሮይተርስ በዘገባው።
በቅርብ ዓመታት በምዕራብ አፍሪካ የሳህል አካባቢ እስከ ምሥራቅ አፍሪካ የተከሰቱ ግጭቶች እንዲሁም ድርቅ እና ጎርፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከቀያቸው አፈናቅለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ባለፈው ዓመት የተፈናቃዮች ቁጥር በ15 በመቶ ጨምሮ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት 44 ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
የአገራት መሪዎች በጉባኤው ላይ በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ስላለው ግጭት እንዲሁም እአአ 2021 እና 2022 ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በተከናወነባቸው በማሊ፣ በቡርኪና ፋሶ፣ በጊኒ እና በሱዳን ስላለው የደኅንነት ሁኔታ ገለጻ ይደረግላቸዋል ሲሉ ሁለቱ ዲፕሎማቶች ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ከደኅንነት ጉዳዮች በተጨማሪ የጉባዔው ተሳታፊዎች በአህጉሪቱ በርካቶችን እየጎዳ ስላለው የምግብ እጥረት ውይይት ያደርጋሉ።
በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ከፍተኛ የድርቅ ስጋት አለ። በተለይ ለአምስት ወቅቶች ዝናብ ያላገኘችው ሶማሊያ በረሃብ አፋፍ ላይ መሆኗን የተባበሩት መንግሥታት ገልጾ ነበር።
ድርጅቱ ከ200 ሺህ በላይ ሶማሊያውያኑ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን እና በረሃብ እየሞቱ ያሉ ሰዎች መሆናቸውን ገልጾ ነበር።
ድርጅቱ ይህ አሃዝ ወደ 700ሺህ ከፍ ሊል እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, Fana BC
ቅዳሜ በሚጀምረው በ36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርልስ ሚሸል ተሳታፊ እንደሚሆኑ ሮይተርስ ዘግቧል።
በጉባዔው ተሳታፊ ለመሆን በርካታ መሪዎች አዲስ አበባ መግባት መጀመራቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በውይይቱ ለመሳተፍ ቀድመው እዲስ አበባ ከደረሱ የአገራት መሪዎች መካከል የደቡብ ሱዳን፣ የሩዋንዳ፣ የጊኒ ቢሳዎ፣ የሌሴቶ፣ የሊቢያ፣ የታንዛኒያ፣ የዴሞክራቲክ ኮንጎ እና የኮትዲቯር መሪዎች ይገኙበታል።












