ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የ71 ዓመቱ አዲሱ የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ቃል መሃላ ሊፍፅሙ ነው
የአፍሪካ ትልቋ ዲሞክራሲ የሚል ስም ያላት ናይጄሪያ አዲሱን መሪዋን ዛሬ ሰኞ በይፋ ትሾማለች።
የ71 ዓመቱ ቲኑቡ ባለፈው የካቲት የተካሄደውን ምርጫ ሲያሸንፉ በናይጄሪያ አዲስ ተስፋ ለመፈንጠቅ ቃል ገብተው ነበር።
ነገር ግን የሚጠብቃቸው ምጣኔ ሃብታዊና የፀጥታ ችግር ቀላል አይደለም።
ሁለት ጊዜ የናይጄሪያን ምርጫ አሸንፈው ሃገሪቱን የመሩት ሙሐሙዱ ቡሐሪ የኑሮ ውድነት፣ ዕዳና አፈና የበዛባት ናይጄሪያን ለተተኪያቸው ያስረክባሉ።
በምርጫው ከቲኑቡ ጋር አንገት ለአንገት ተያይዘው የነበሩት ሁለቱ ተቀናቃኞች ውጤቱ ተጭበርብሯል በሚል ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውታል።
ለስምንት ዓመታት ሃገሪቱን የመሩት ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ቡሐሪ ግን ውጤቱ “ተዓማኒ” ነበር የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ደግሞ “ነፃና ፍትሐዊ” ነው ይላሉ።
የደቡብ አፍሪካዊውን ሲሪል ራማፎሳ ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች በመዲናዋ አቡጃ በሚካሄደው በዓለ-ሲመት ይታደማሉ።
ነገር ግን አዲሱ ፕሬዝደንት ለፌሽታ የሚሆን ጊዜ ያላቸው አይመስልም። ናይጄሪያዊያን አዲሱ መሪ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባ ነው የሚፈልጉት።
የዋጋ ግሽበት ካለፉት 18 ዓመታት ከታየው በላይ ሆኖ ዜጎችን አስጨንቋል። ከሶስት ናይጄሪያዊያን አንዱ ሥራ አጥ ነው። ሃገሪቱ የምትተማንበት የነዳጅ ኢንዱስትሪም እየኮሰመነ ነው።
አዲሱ መሪ፤ ለሳቸው ድምፃቸውን ያልሰጡ ሰዎችን ለማሳመን በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ብዙ ሥራ መሥራት አለባቸው።
ነገር ግን በሙያቸው የሂሳብ ሠራተኛ የሆኑት አዲሱ ፕሬዝደንት በፈተናዎች የሚገቱ አይመስሉም።
ሌጎስን ሁለት ጊዜ በሃገረ-ገዥነት ያስተዳደሩት ቲኑቡ የናይጄሪያ የንግድ ማዕከል የምትባለውን ከተማ አዘመውነዋታል። ከፊት የሚጠብቃቸው ሥራም ቀላል እንደማይሆን ያውቁታል።
የአዲሱ ፕሬዝደንት ባለሟሎች ከ200 ሚሊዮን ባለይ ሕዝብ ያላት ናይጄሪያን ለማስተዳደር አቅም ያላቸው ሰው ናቸው ሲሉ ይመስክሩላቸዋል።
በሌላ በኩል ነቃፊዎቻቸው ደግሞ ሌጎስ ለማዘመን ጉልበት የተቀላቀለበት መንገድ መጠቀማቸውን በማስታወስ ሰውዬው ብቁ አይደሉም ይላሉ።
አልፎም ከምርጫው በኋላ ሁለት ጊዜ ውጭ ሃገር መጓዛቸው የጤናቸው ነገር እንዴት ነው የሚል ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል።
ከሁለት ዓመት በፊት ምንነቱ ላልታወቀ በሽታ ሕክምና ለማግኘት ለንደን ወራት ከርመው ነው የተመለሱት።
ይህ ጥያቄ የተሰነዘረላቸው አዲሱ ፕሬዝደንት ጉዳዩን ቸል በማለት ይህ ሥራ የኦሊምፒክ አትሌት መሆን አይጠይቅም ብለዋል።
የቲኑቡ የቅርብ ሰዎች የዕድሜ ጉዳይ ሲነሳ ‘ጆ ባይደን አሉ አይደል በ80 ዓመታቸው’ የሚል ምላሽ መስጠት ይቀናቸዋል።
ምንም እንኳ አዲሱ ፕሬዝደንት ዛሬ ቃለ-መሐላ ቢፈፅሙም የምርጫውን ጉዳይ የሚከታተለው ፍርድ ቤት ከነገ ጀምሮ ይሰየማል።