ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሐማስ ታጋቾችን የሚለቀው በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት መሆኑን አስታወቀ
ሐማስ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ታጋቾችን መልቀቅ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
ይህን የሐማስ ውሳኔ ተከትሎ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ፈርሶ ድጋሚ ጦርነት ሊጀምር ይችላል የሚለው ስጋት ቀንሷል።
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን በግብፅ ከተካሄደ ውይይት በኋላ በሰጠው መግለጫ የግብፅ እና የኳታር አደራዳሪዎች "እንቅፋቶችን ያስወግዳሉ" ብሏል።
የግብፅ እና የኳታር አደራዳሪዎችም ተፈጥሮ የነበረው አለግባባት መፈታቱን አስታውቀዋል።
የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ባይሰጡም ቡድኑ በሚቀጥለው ቅዳሜ ሶስት ታጋቾችን የማይለቅ ከሆነ ጦርነት ይጀመራል ብለዋል።
ሐማስ፤ እስራኤል ስምምነቱን ጥሳለች በሚል ታጋቾችን እንደማይለቅ ማስታወቁን ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፈው ማክሰኞ ጦርነት ይጀመራል የሚል ዛቻ አሰምተው ነበር።
ሐማስ፤ መጠለያዎችን ጨምሮ አስፈላጊ የሆኑ ሰብዓዊ እርዳታዎች እንዳይደርሱ አድርጋለች ሲል ነው እስራኤልን የከሰሰው። እስራኤል የሐማስን ወቀሳ ታስተባብላለች።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል ስምምነቱን እንድታቋርጥ ሐሳብ አቅርበው "ሁሉም ታጋቾች ቅዳሜ የማይፈቱ ከሆነ ገሀነም ይወርዳል" ማለታቸው ይታወሳል።
ቤንያሚን ኔታኒያሁ የትራምፕን ዱካ ተከትለው "ሐማስ በሚመጣው ቅዳሜ ቀትር ስደተኞችን የማይለቅ ከሆነ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ይቋረጣል። የእስራኤል ኃይል ሐማስን እስከሚረታ ድረስ ይዋጋል" ብለዋል።
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ 67ቱም ታጋቾች እንዲለቀቁ አሊያም በስምምነቱ መሠረት ሶስት እንዲለቀቁ ስለመጠየቃቸው ግልፅ አይደለም።
ረቡዕ ዕለት የግብፅ የደኅንነት ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግብፅ እና ኳታር "የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማዳን የሚቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው።"
በጋዛ የሐማሱ መሪ ኻሊል አል-ሐያ ወደ ካይሮ አቅንተው ከግብፅ የደኅንነት ሰዎችና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር መምከራቸውን ምንጮቹ ገልፀዋል።
ሐማስ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ ትኩረቱ የስምምነቱ አንቀፆች እንዲተገበሩ በተለይ ደግሞ መጠለያዎች፣ የግንባታ ዕቃዎች፣ የሕክምና መሣሪያዎች እና ነዳጅ እንዲቀርብ እንደሆነ ተናግሯል።
"በተያያዘ ሐማስ ስምምነቱን ለመተግበር ቁርጠኛ ነው። በዚህም መሠረት በተቀመጠው መርሐ ግብር የእስረኞች ልውውጥ ማድረጉን ይቀጥላል" ይላል መግለጫው።
የግብፅ መንግሥት ጣቢያ የሆነው አል ቃሔራ ቴሌቪዥን እንዲሁም ዋና መሥሪያ ቤቱን ኳታር ያደረገው አል ጀዚራ በካይሮ የተካሄደው ውይይት ስኬታማ እንደነበር ዘግበዋል።
ነገር ግን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቢሮ ዋቢ አድርገው የአልጀዚራን ዘገባ "ሐሰተኛ" ነው ብለውታል።
የጋዛ ነዋሪዎች ጦርነት ድጋሚ ሊጀመር ይችላል የሚል ስጋት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
"የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሲፈርም እጅግ ደስ ብሎን ነበር። ነገር ግን አሁን የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ ነጋዴዎች የሸቀጥ ዋጋ ከፍ ማድረግ ጀምረዋል" ሲል ሙቲ አል-ቄድራ ለቢቢሲ አረብኛው ጋዛ ላይፍላይን ፕሮግራም ተናግሯል።
"አላህ ዘላቂ ሰላም እንዲያመጣ ነው ፀሎቴ። በተለይ ደግሞ የአል-ቄድራ ቤተሰብ አባል የሆኑ 65 ሰዎችን ከተሰዉብኝ በኋላ። አሁን ቀውሱ ተወግዷል። ሌሎች ሰዎች መስዋዕት እንደማይሆኑ ተስፋችን ነው።"
በቱኩስ አቁም ስምምነቱ መሠረት ስድስት ሳምታት በሚቆየው በመጀመሪያው ዙር 33 እስራኤላዊያን የሚለቀቁ ሲሆን እስራኤል ደግሞ 1900 ፍልስጤማዊያንን ትለቃለች።
እስካሁን 16 በሕይወት ያሉ እስራኤላዊያን ሲለቀቁ ሐማስ በፈቃዱ አምስት ታይላንዳዊያን ስደተኞችን ለቋል።
በሁለተኛው ዙር ስምምነት ሁሉም እስራኤላዊያን ከጋዛ የሚለቀቁ ሲሆን እስራኤል ሙሉ በሙሉ ወጥታ ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚፈረም ይጠበቃል። ነገር ግን የሁለተኛው ዙር ስምምነት ድርድር ገና አልተጀመረም።