ዩኬ በህገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች እና ተሳታፊ በሚሆኑ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ልትጥል ነው

በትንሽ የፕላስቲክ ጀልባ ላይ የተሳፈሩ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዩናይትድ ኪንግደም ህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ላይ ማዕቀብ ለመጣል ባስተዋወቀችው አዲስ አሰራር፤ የውንብድና ቡድን መሪዎች፣ ሙሰኛ ባለስልጣናት እና የፖሊስ መኮንኖች እንዲሁም የሀሰት ፓስፖርት ነጋዴዎች እና ትናንሽ ጀልባዎችን የሚያቀርቡ ግለሰቦች ስማቸው በይፋ ተጠቅሶ ሊዘረዘሩ እንደሚችል ተገለጸ።

የመጀመሪያ እርምጃዎቹ ረቡዕ ዕለት ይፋ የሚደረጉለት ይህ እቅድ፤ የሀገሪቱ መንግስት ከዚህ ድርጊት ጀርባ ያሉ የወንጀል መረቦችን ለመበጣጠስ የያዘው እቅድ ዋነኛ አካል ተደርጎ ተወስዷል።

በማዕቀቡ እቅድ መሰረት፤ ግለሰቦች እና ኩባንያዎች ንብረታቸው እንዳይቀሳቀስ ሊታገድ፣ የጉዞ እገዳ ሊጣልባቸው እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ገደብ ሊጣልባቸው እንደሚችል ይጠበቃል።

በዚህ እርምጃ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውስጥ፤ ህገ ወጥ የሰው ዝውውሩን በማመቻቸት ወይም ትርፍ በማግኘት የተከሰሱ ከ20 በላይ ሰዎች እንደሚካተቱ ተነግሯል።

የስደተኞች አማካሪ ኮሚቴ ግን እርምጃው የሚፈጥረው ተጽዕኖው ውስን ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።

የኮሚቴው ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ማዴሊን ሳምፕሽን፤ እገዳዎቹ "በጥቅሉ በኢንዱስትሪው ላይ እንዲሁም ለአነስተኛ ጀልባዎች የጉዞ መስመር ህልውና ላይ መሰረታዊ ለውጥ" የሚያመጣ የሚሆን ከሆነ፤ "እንደሚደነቁ" ተናግረዋል።

"ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሳተፉት ሰዎች በጣም ብዙ ሰዎች ስለሆኑ በግለሰብ ደረጃ ዒላማ ማድረግ የሚኖረው ተጽዕኖ ጥልቅ ላይሆን ይችላል" በማለት በቢቢሲ ሬዲዮ 4 ለሚተላለፈው ቱደይ ፕሮግራም ተናግረዋል።

"የሰው አዘዋዋሪዎች የሚንቀሳቀሱባቸው ሌሎች ሀገራት ትብብር የእርምጃው የሚኖረው ተጽዕኖ በተወሰነ ደረጃ ይወስናል" ሲሉም አክለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ረቡዕ ዕለት የሚወጣው የመጀመሪያ ዝርዝር፤ ዩናይትድ ኪንግደም በረጅም ጊዜ ሂደት የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም በምታደርገው ጥረት፤ ምን አይነት ግለሰቦችን ዒላማ እንደምታደርግ ለማሳየት ያቀደ ነው። ሙሰኛ ባለስልጣናትን እና የፖሊስ መኮንኖችን የሚያካትቱ ተጨማሪ የማዕቀብ እርምጃዎች ይፋ ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ባለፈው ዓመት ለምርጫ በተወዳደሩበት ወቅት፤ ሰው አዘዋዋሪ ወንበዴዎችን ለማጥፋት እና ህገወጥ ስደትን ከምንጩ ለማስቆም ቃል ገብተዋል።

መንግሥት እንደሚገልጸው የወንጀል ቡድኖች የሚጫወቱት ተጋላጭ በሆኑ ሰዎች ተስፋ ነው። ነገር ግን መንግስት የሚጥለው ማዕቀብ ዓለም አቀፍ ባህሪ ባላቸው የዝውውር መረቦች ላይ እንዴት ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችል ጥያቄዎች ተነስተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ፤ የማዕቀብ ስርዓቱ "በፕላኔቷ ላይ በየትኛውም ቦታ በዓይነቱ የመጀመሪያው" ያሉ ሲሆን የወንጀል ቡድኖች "የተጋለጡ ሰዎችን ያለ ቅጣት" የሚበዘብዙበትን" ሁኔታ ለማስቆም ቁልፍ እርምጃ መሆኑን አስረድተዋል።

"እኛ እየመራን ነው፣ ሌሎች ይከተላሉ" ሲሉ በቢቢሲ ሬዲዮ 4 ቱደይ ፕሮግራም ተናግረዋል።

ማዕቀቡ፤ ከወንጀል ድርጊቱ መሪዎች በተጨማሪ መደበኛ ያልሆነ ስርዓት በመጠቀም በሀዋላ የገንዘብ ዝውውር እንደሚያደርጉ የፋይናንስ ደላሎች ያሉ አመቻቾችን ዒላማ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ባለስልጣናት ገለጻ፤ አዲሶቹ ማዕቀቦች "መደበኛው የህግ ማስከበር እና የወንጀል ፍትህ ስርዓት ሊደርሱ በማይችሉባቸው" የሰው ዝውውር ወንጀል ቡድኖችን እንቅስቃሴዎች ላይ ያነጣጥራሉ።

የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዬቬት ኩፐር፤ አዲሱ የማዕቀብ ስርዓት "በሰው ልጅ መከራ ትርፍ የሚያገኙ የወንጀል ቡድኖች ላይ ለምናደርገው ትግል ወሳኝ እርምጃ ነው" ብለዋል።

"የሰዎች አዘዋዋሪዎች የገንዘብ ምንጭን በማቋረጥ እና መረቦቻቸውን አንድ በአንድ በመበጣጠስ፤ በሚንቀሳቀሱበት ቦታ ሁሉ ንብረታቸውን እና ስራዎቻቸውን ዒላማ ለማድረግ ያስችለናል" ብለዋል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው በተያዘው አውሮፓውያኑ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ከ20,000 በላይ ሰዎች በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ተሻግረዋል።

ይህ ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ወደ 50 በመቶ ገደማ ጭማሪ አለው ተብሏል።