የ18 ዓመቱ ወጣት በትንሽ ዕድሜው ከንቲባ ሆኖ የተመረጠ ጥቁር አሜሪካዊ ሆነ

ታትሟል

የ18 ዓመቱ የኮሌጅ ተማሪ በአሜሪካ የቴኔሲ ግዛት ውስጥ የምትገኝ አንስተኛ ከተማ ከንቲባ ሆኖ በመመረጥ ክብረ ወሰን ያዘ።

በዚህም ለጋው ጄይለን ስሚዝ በአሜሪካ ታሪክ በዕድሜ ትንሹ ከንቲባ ሆኖ የተመረጠ ጥቁር አሜሪካዊ እንዲሆን አስችሎታል።

ተመራጩ ወጣቱ ከንቲባ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነው።

ጄይለን ከሜምፊስ ከተማ 48 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘው የኧርል ከተማ ከንቲባ እንዲሆን የተመረጠው ባለፈው ማክሰኞ ዕለት ነው።

ከምርጫው ውጤት በኋላ “እናቴ በደስታ ማልቀስ ማቆም አልቻለችም” ሲል ከንቲባ ሆኖ የተመረጠው ዴሞክራቱ ወጣት ለዋሽንግተን ፖስት ተናግሯል።

ጄይለን ስሚዝ 1ሺህ 800 ነዋሪ ያላትን ከተማ እንዲመራ ከተመረጠ በኋላ፤ “በኧርል የተሻለ ምዕራፍ መገንባት የምንጀምርበት ጊዜ ነው” ሲል የፌስቡክ ገጹ ላይ ጽፏል።

ወጣቱ ፖለቲከኛ የከተማዋ ከንቲባ ሆኖ እንዲመረጥ ድምጽ ለሰጡት ሰዎች ምስጋናውንም አቅርቧል።

የአዲሱ ከንቲባ የምርጫ ቅስቀሳ አጀንዳዎች የነበሩት የፖሊስ ኃይልን ማጠናከር፣ የከተማዋን የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ማደስ፣ እንዲሁ ለተተዉ ቤቶች መፍትሄ መስጠት እና የማኅብረሰብ ተሳትፎን ማጠናከር የሚሉት ይገኙበታል።

አዲሱ ከንቲባ በተከማዋ ትልቅ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብር መክፈት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ገልጿል።

ባለ1800 ነዋሪ ከተማ ከዚህ ቀደም የነበራት ትልቅ መደብር ከተዘጋ ዓመታት አልፈዋል።

ጄይለን ስሚዝ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ የተማሪዎች ፕሬዝዳንት ሆኖ አገልግሏል።

“አሁን ላይ ከንቲባ መሆን እየቻልኩ 30 ወይም 40 እስከሆን መጠበቅ አልፈለኩም” ሲል ለዋሽንግተን ፖስት ተናግሯል።

ወጣቱ ፖለቲከኛ ለከንቲባነት ሲወዳደር የሊትል ሮክ ከተማ መሪ ከሆኑት አፍሪካ አሜሪካሪዊው ፍንክ ስኮት ጁኒየር ምክርን ሲቀበል ነበር።

“ጄይለን የመጀመሪያው ወጣት ጥቁር አሜሪካዊ ከንቲባ ሆኖ በመመረጡ በእርሱ እና በአጠቃላይ ኧርል ማኅብረሰብ በጣም ተደስቻለሁ” ሲሉ ስኮት ለሲኤንኤን ተናግረዋል።

ስሚዝ የከንቲባ ኃላፊነቱን እየተወጣ በአርካንሳስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሚድ-ሳውዝ ትምህርቱን የመቀጠል ዕቅድ እንዳለው ያስታወቀ ሲሆን፣ ወደፊት ዐቃቤ ሕግ የመሆን ፍላጎት እንዳለው ጨምሮ ተናግሯል።

እአአ 2015 ላይ ማይክል ሴሽንስ የተባለ ነጭ አሜሪካዊ የ18 ዓመት ወጣት በሚቺጋን ላለች ከተማ ከንቲባ ሆኖ ተመርጦ ነበር።

ወጣቱ የሂልሳይድ ከተማ ከንቲባ ሆኖ ቃለ መሃላ ሲፈጽም ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አላጠናቀቀም ነበር።

የትምህር ቤቱ ርዕስ መምህር “ከንቲባ ሆኖ ቢመረጥም የቤት ሥራውን ሳይሰራ መምጣት እንደማይችል ነግሬው ነበር። የከተማዋን ኃላፊ ከትምህርት ቤት ማባረርን አልፈልግም” ሲሉ የሰጡት አስተያየት ብዙዎችን ፈገግ ያስባለ ነበር።