ፕሬዚዳንት ፑቲን በጦር መሳሪያ አቅርቦት ችግር ምክንያት ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሩን አባረሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን የጦር መሳሪያ ሎጂክስቲክስን ይመሩ የነበሩትን የመከላከያ ምክትል ኃላፊን አባረሩ።
ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሩ ጄኔራል ዲሚትሪ ቡልጋኮቭ ካጋጠመው የጦር መሳሪያ አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ ምክንያት ቅዳሜ ዕለት ከኃላፊነታቸው መነሳቻውን የመከላከያ ሚኒስቴር በቴሌግራም አስታውቋል።
የ67 ዓመቱ ሚኒስትር ወደ ሌላ የኃላፊነት ስራ እንደተሸጋገሩም ተገልጿል።
በሞስኮ የወደብ ከተማ ማሪፖል ላይ ጭካኔ የተሞባለበት ከበባ በመምራት የሚታወቁት ኮሎኔል ጄኔራል ሚካሂል ሚዚንትሴቭ ይተኳቸዋል።
ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሩ ከአውሮፓውያኑ 2008 ጀምሮ የሩሲያን ወታደራዊ የሎጂስቲክ ተግባራትን በኃላፊነት ሲመሩ የቆዩ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2015 የሩሲያ ወታደሮች ወደ ሶሪያ መሰማራታቸውን ተከትሎም የሩሲያ ወታደሮችን ማቅረብ ዋነኛ ተግባራቸው ሆኖ ቆይቷል።
ነገር ግን ከቅርብ ወራት ወዲህ በሞስኮ ገሸሽ እንደተደረጉ እየተነገረ ነው። ለዚህም የሎጂስቲክ ዘመቻቸው ቀውስ የተሞላበት ነበር ይህም የሩሲያን ግስጋሴ በማደናቀፍ ወታደሮቻቸው አቅርቦት እንዳይኖራቸው ምክንያት ሆኗል በማለት ተጠያቂ አድርገዋቸዋል።
በቅርብ ወራት ሩሲያ ሁለቱን አጋሮቿን ሰሜን ኮሪያ እና ኢራንን ለከባድ ጦር መሳሪያዎች እንዲሁም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እንዲሸጡላት ለመጠየቅ ተገዳለች።
በማህበራዊ ድረጾች ላይ አዲስ የሩሲያ ምልምል ወታደሮች የዛገ ጠመንጃ ታጥቀው የታዩ ሲሆን ከጄኔራል ዲሚትሪም መባረርም ጋር ተገጣጥሟል።
በሩሲያ የጦር ደጋፊዎች የጄኔራሉ ከኃላፊነታቸው መነሳት እንዲሁም የማሪፖልን ከበባ በመመምራት ማዕቀብ የተጣለባቸው የጄኔራል ሚካሂል ሹመትን በበጎ አይተውታል።
በበርካታ ዩክሬናውያን ዘንድ “የማሪፖል አራጅ” እየተባሉ የሚጠሩት ጄኔራል ሚካሂል ሚዚንትሴቭ በሶሪያ ላይ የነበረውን የሩሲያን ጦር የመሩ ሲሆን በአሌፖ ከተማ የደረሰውን አሰቃቂ የቦምብ ጥቃት በማቀነባበር ይከሰሳሉ።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በዩክሬን እና በሶሪያ ጦርነቶች “የሚያስወቅሱ ተግባራትን” እና “ጭካኔዎችን” ፈፅመዋል በሚልም ነው በ60 ዓመቱ ጄኔራል ላይ ማዕቀብ የጣለባቸው።












