ባይደን በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ተማሪዎች የ10 ሺህ ዶላር እዳ ሰረዙ

ታትሟል

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን የትምህርት ቤት እዳ እንደሚሰርዙ ተገለጸ።

ከፌደራል መንግሥቱ የተመደበላቸውን ወደ 10 ሺህ ዶላር የሚጠጋ እዳ ነው የሚሰርዙት።

በዚህ እዳ ስረዛ የሚካተቱት በዓመት ከ125 ሺ በላይ ገቢ የሚያገኙ አሜሪካውያን ናቸው።

ከፍተኛ የገንዘብ ድጎማ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች በተዘጋጀ ፕሮግራም ሥር ላሉ ተማሪዎች ደግሞ 20 ሺህ ዶላር እዳ ይሰረዛል።

“ከዚህ በኋላ የተማሪ እዳ ሸክም አይሆንባችሁም” ብለዋል ባይደን።

ወደ 43 ሚሊዮን የሚጠጉ አሜሪካውያን 1.6 ትሪሊዮን ዶላር የተማሪ እዳ አለባቸው።

ከእነዚህ መካከል አንድ አምስተኛው ከ10 ሺህ ዶላር በላይ እዳ ነው ያለባቸው።

በ2020 አጋማሽ በጊዜያዊነት ቆሞ የነበረው የእዳ ክፍያ እስከዚህ ዓመት ማገባደጃ እንደሚቆይ ተገልጿል።

ባይደን የእዳ ስረዛ ውሳኔያቸው አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው “የእፎይታ ጊዜ” የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

“ጫናው ከፍተኛ ስለሆነ ከተመረቃችሁ በኋላ የመካከለኛ መደብ ኑሮ ለማግኘት ትቸገራላችሁ። በአንድ ወቅት የኮሌጅ ዲግሪ ያለው ሰው ኑሮው ከመካከለኛው መደብ ይመደብ ነበር” ብለዋል።

ባይደን እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ተራማጅ ዴሞክራቶች ያሳደሩትን ጫና ተከትሎ ዋይት ሀውስ ውስጥ ስለ እዳ ስረዛ ከፍተኛ ክርክር ከተደረገ በኋላ ነው።

እዳ እንዲሰረዝ ከፍተኛ ጫና ካሳደሩ መካከል ሴናተሮቹ ኤልዛቤት ዋረን እና ቻክ ሹመር ይገኙበታል።

ዕቅዳቸው ከእያንዳንዱ ባለ እዳ 50 ሺህ ዶላር ማስቀነስ ነበር።

አሁን የተላለፈው ውሳኔ ግን ከእያንዳንዱ ባለ እዳ አንድ ጊዜ 10 ሺህ ዶላር የመቀነስ ነው።

ይህም መንግሥትን 300 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስወጣው ይገመታል።

ባይደን ውሳኔው “የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ያማከለ ነው” ሲሉ ተከራክረዋል።

“ሠርቶ አደር አሜሪካውያንን በመርዳቴ አልጸጸትም። ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ ዜጎች የዚህ እዳ ስረዛ ተጠቃሚ አይሆኑም” በማለትም አክለዋል።

ሪፐብሊካኖችና ለዘብተኛ ዴሞክራቶች የእዳ ስረዛው በአሜሪካውያን ኪስ ተጨማሪ ገንዘብ በማስገባት የኑሮ ውድነትን ያባብሳል ሲሉ ተደምጠዋል።

ሪፐብሊካኑ ኬቨን ማካርቲ “ለባይደን የእዳ ስረዛ ገንዘብ የሚመጣው ከየት ነው? ብላችሁ ብትጠይቁ፣ መልሱ የተማሪ እዳቸውን ከከፈሉ ዜጎች ነው። እነዚህ ትጉህ አሜሪካውያን የተማሪ እዳ የከፈሉ ወይም ከመጀመሪያውም ገንዘብ ያልወሰዱ ናቸው። ታዲያ ለምን በእዳ ስረዛ ስም ገንዘባቸው ይወሰዳል?” ሲሉ ተችተዋል።

በሌላ በኩል ዴሞክራቶች እንደሚሉት፣ የእዳ ስረዛው በዘር ምክንያት የሚፈጠረውን የገቢ አለመመጣጠን የሚያጠብ ነው ብለው ተከራክረዋል።

በብዛት ከፌደራል መንግሥቱ ገንዘብ የሚበደሩት ጥቁር አሜሪካውያን ተማሪዎች ናቸው።

ዲግሪ ሲማሩ ለአራት ዓመታት ከመንግሥት የተበደሩት ገንዘብ ወደ 25 ሺ ዶላር እዳ ይሆናል።

ይህም ከነጭ አሜሪካውያን ተማሪዎች የበለጠ እንደሆነ ይገለጻል።