በካርቱም ሕዝብ በሚበዛበት ገበያ ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት በርካቶች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ትናንት እሑድ ከፍተኛ ሕዝብ በሚገኝበት የገበያ ቦታ በደረሰ የቦምብ የአየር ጥቃት በርካቶች ተገደሉ።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በትንሹ 35 ሰዎች ሲገደሉ ከ60 በላይ ቆስለዋል ብሏል።
ቁዋሮ ገበያ በሚል የሚታወቀው ይህ ክፍት የገበያ ማዕከል የሚገኘው በደቡባዊ ካርቱም ነው።
በገበያ ስፍራው በርካቶች የተገደሉት ተቀጣጣይ ቦምቡ ከወታደራዊ አውሮፕላን ከተጣለ በኋላ ነው።
ሁለቱ ተቀናቃኝ ታጣቂዎች ካለፈው ሚያዚያ ጀምሮ በውጊያ ላይ ናቸው።
ሱዳን ላለፉት ስድስት ወራት በጦርነት ብትሆንም ትናንት የደረሰው ግድያ የሆስፒታል እርዳታ ሰጪዎችን እንደ አዲስ ያስደነገጠ ነበር ብለዋል የድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን አስተባባሪ ማሪ በርተን በኤክስ ሰሌዳቸው።
“አካላቸውን ያጡ ሰዎችን ሕይወት ለማዳን እየተሯሯጥን ነው። ጥቃቱ እጅግ አሰቃቂ ነበር” ብለዋል።
የድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን ባልደረባ ሎሬታ ቻርለስ በባሺር ቲቺንግ ሆስፒታል ውስጥ ቦምቡ ክፉኛ የጎዳቸውን ሰዎች በስቃይ ውስጥ ሆነው ለመርዳት እየሞከሩ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንዳንዶች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ50 በላይ እንደሆነ ይናገራሉ።
ሱዳን ወደለየለት የእርስ በእርስ ግጭት የገባችው ባለፈው ሚያዝያ ሲሆን የሠራዊቱ መሪ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ደጋሎ በመከላከያ ሠራዊት የወደፊት ጥምረት ላይ ባለመግባባታቸው የተጀመረ ነበር።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ አምስት ሚሊዯን ሱዳናዊያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
ካርቱም እና ዙሪያዋ እንዲሁም ምዕራብ ዳርፉር ክፉኛ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች ናቸው።
ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ደጋሎ የሚመሩት የፈጥኖ ደራሹ ኃይል አብዛኛውን ካርቱምን፣ ኦማዱርማንን እና ባሕሪን እንደተቆጣጠረ ይነገራል።
የአልቡርሃን ሠራዊት እነዚህን ቦታዎች ለመቆጣጠር በርካታ የአየር ጥቃቶችን ያካሄዳል።
ከሳምንት በፊት በነበረ የአየር ጥቃት 20 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ ሕጻናት ነበሩ።
አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎች አገሮች ሁለቱን ተዋጊዎች ለማግባባት ብዙ ሞክረዋል ግን አልተሳካላቸውም።
ተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ተደርገውም በተደጋጋሚ ተጥሰዋል።












