ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንድ የታንዛኒያ ባለሥልጣን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባወጡት ጽሁፍ ከሥራ ተባረሩ
አንድ የታንዛኒያ መንግሥት መሥሪያ ቤት ኃላፊ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መንግሥት ተግባራዊ ያደረገውን የገንዘብ ዝውውር ግብር በመቃወም በመጻፋቸው ከሥራቸው ተባረሩ።
የታንዛኒያ መንግሥት ዜጎች በሞባይል አማካይነት ገንዘብ ሲያስተላልፉ ለመንግሥት የሚከፈል ግብር እንዲኖረው ማድረጉን በመቃወም ነው ግለሰቡ ሃሳባቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጻፉት።
በታንዛኒያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ክልላዊ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ጆናስ አፉምዊስዬ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተቃውሟቸውን ከገለጹ በኋላ ከሥራቸው መሰናበታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሷቸዋል።
ጆናስ የሥራ ስንብት ደብዳቤውን መቀበላቸውን አረጋግጠዋል፣ ደብዳቤው ግለሰቡ ከሥራቸው የተባረሩት በአውሮፓውያኑ 2003 የወጣውን የአገሪቱን የመንግሥት ሠራተኞች አገልግሎት ሕግን በመተላለፋቸው መሆኑን ጠቅሷል።
ነገር ግን ጆናስ በመባረራቸው ላይ ለአገሪቱ የመንግሥት ሠራተኞች ኮሚሽን ይግባኝ እንደሚል ተናግረዋል።
ደብዳቤው ለግለሰቡ ከሥራቸው መባረር ምክንያት የተባለው የተቃውሞ ጽሁፍ በየትኛው የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንደወጣ በግለጽ ያስቀመጠው ነገር የለም።
ከዚህ በተጨማሪም ግለሰቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ በሚያወጧቸው ጽሁፎች መንግሥት የሚያካሂደውን የክትባት ዘመቻ በመቃወም እና የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁን ስም በማጥፋት ተከሰዋል።
የአገሪቱ ሠራተኞች ማኅበር ኃላፊ የሆኑት ቱማይኒ ኒያምሆካያ፣ የጆናስ ከሥራው መባረርን በተመለከተ ግለሰቡ ሐሳባቸውን የመግለጽ መብት አላቸው በማለት እርምጃውን ተቃውመው ‘ዘ ሲቲዝን’ ለተባለው ጋዜጣ አስተያየት ሰጥተዋል።
ታንዛኒያ በተለይ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ የሥልጣን ዘመን የመናገር ነጻነት እየተገደበባት እንደሆነ እና በመንግሥት ላይ ትችት የሚሰነዝሩትን በማሰደድ ስትወቀስ ቆይታለች።