ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፌስቡክ ጽሑፍ ያጋራው ግብፃዊ ተመራማሪ የሦስት ዓመት እስር ተፈረደበት
የግብፅ ፍርድ ቤት በግል የፌስቡክ ገጹ ላይ ጽሑፍ ያጋራውን ተመራማሪ በሦሰት ዓመት እስር እንዲቀጣ ወሰነ።
ፍርድ ቤቱ አሕመድ ሳሚር ሳንታውያ የተባለው የ30 ዓመት ተመራማሪ “ሐሰተኛ ዜና በማጋራት” ጥፋተኛ ነው ካለው በኋላ ነው የእስር ትዕዛዙ የተላለፈበት።
ተመራማሪው ጥፋተኛ ተብሎ ፍርድ የተላለፈበት ይግባኝ መጠየቅ በማያስችል ልዩ ፍርድ ቤት ነው ተብሏል።
የአሕመድ ሳሚር ሳንታውያ ጠበቃ የሆኑት አሕመድ ራግሔብ ደንበኛቸውን ከእሰር ለማስለቀቅ በቅርቡ ለተቋቋመው ፕሬዝደንታዊ ምህረት አድራጊ ኮሚቴ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ 'ማሳ ማስራ' ለተሰኘው ገለልተኛ የዜና ድረ-ገጽ ተናግረዋል።
ይህ ተመራማሪ በዚሁ የፌስቡክ ገጹ ላይ ባጋራው ጽሑፍ ከአንድ ዓመት በፊት የአራት ዓመት እስር ተላልፎበት ነበር።
ይሁን እንጂ የፍርደኛው ጠበቃ ቅሬታ ካቀረቡ በኋላ ይህ የእስር ፍርድ ውድቅ እንዲደረግ ሆኖ ነበር። ሆኖም ተመራማሪው ለአንድ ዓመት ከግማሽ ያክል በእስር ቆይቷል።
በርካታ የግብፅ እና ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች አሕመድ ሳሚር ሳንታውያ ከእስር እንዲለቀቅ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
አሕመድ ሳሚር ሳንታውያ በአውሮፓዊቷ ኦስትሪያ ትምህርቱን እየተከታተለ የነበረ ሲሆን፣ ለእረፍት ወደ ግብፅ ባመራበት ጊዜ ነው ነበር ከ18 ወራት በፊት በቁጥጥር ሥር የዋለው።
በተመራማሪው ላይ የተላለፈው የፍርድ ውሳኔ የተሰማው በግብፅ ፖለቲከኞችን ያሳተፍ የፖለቲካ ምክክር በተጀመረበት ዕለት ነው።
ከዚህ ምክክር ቀደም ብሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው ፖለቲከኞች እና ማኅብረሰብ አንቂዎች ከእስር ተለቀዋል።