ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የመተማመኛ ድምጽ ሊሰጥባቸው ነው

ታትሟል

የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ዛሬ የመተማመኛ ድምፅ ሊሰጥባቸው ነው።

መሰል ጉዳዮችን የሚመረምረው የላይኛው ምክር ቤት ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሰር ግራሃም ብሬዴ ይህን ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣን ይልቀቁ የሚሉ ድምፆች እየበረከቱ መጥተዋል።

ቦሪስ የመተማመኛ ድምፅ ሊሰጥባቸው እንደሆነ የእንግሊዝ መገናኛ ብዙሃን ከውስጥ አዋቂዎች ሰምተናል ሲሉ ነው የከረሙት።

ቦሪስ የመተማመኛ ድምፅ የሚሰጥባቸው 54 የገዥው ወግ አጥባቂ አባላትና የሕዝብ እንደራሴዎች [ቶሪስ] በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ያለን እምነት ተሟጧል የሚል ደብዳቤ ካስገቡ ነው።

ባለፈው ሰንበት የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ግራንት ሻፕስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመተማመኛ ድምፅ ቢወጣባቸውም ምንም እንደማይሆኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፉት 10 ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከገዛ ፓርቲያቸው ያለመተማመን ድምፅ ሊሰጥባቸው እንደሚችል ሲነገር ቆይቷል።

እስካሁን 28 ቶሪዎች [የገዥው ፓርቲ አባላትና የሕዝብ እንደራሴዎች] ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እንዲለቁ በይፋ ጠይቀዋል።

ቦሪስ በንግሥት ኤልሳቤጥ 70ኛ ዓመት የፕላቲኒዬም ኢዩቤልዩ ክብረ በዓል ላይ ሲገኙ ሕዝቡ ቁጣን ገልጦባቸዋል።

የመተማመኛ ድምፅ እንዴት ነው የሚሠራው?

በገዥው ወግ አጥባቂ ፓርቲ ሕግ መሠረት ቢያንስ 15 በመቶ የፓርቲው አባላትና የሕዝብ እንደራሴዎች ድምፅ መስጠት አለባቸው።

ገዥው ፓርቲ በአሁኑ ወቅት በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት 54 አባላት አሉት።  

እኒህ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩን አንደገፍም ብለው ደብዳቤ መፃፍ አለባቸው።

እስካሁን ምን ያህል አባላት ደብዳቤ እንዳስገቡ ግልፅ አይደለም።

54ቱም አባላት ደብዳቤ ካስገቡ ከፍተኛ ቶሪዎች በመሪያቸው ላይ በድብቅ የተማመኛ ድምፅ ይሰጣሉ።

ይህ ከሆነ በኋላ ጉዳዩ ወደ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አምርቶ 180 አባላት አንተማመንም የሚል ድምፅ መስጠት አለባቸው።

ቦሪስ ይህን የመተማመን ድምፅ ማለፍ ከቻሉ ሌሎችንም ፈተናዎች የማለፍ ዕድላቸው የሰፋ ነው።