የእስራኤል ጦር በአንድ ቀን ብቻ 24 ወታደሮቹ በጋዛ መገደላቸውን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእስራኤል ጦር በአንድ ቀን ውስጥ 24 ወታደሮቹ መገደላቸውን አስታወቀ።
በ24 ሰዓታት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእስራኤል ወታደሮች ሲገደሉ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የአገሪቱ ጦር ትናንት በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር፣ ከሰዓት በኋላ ሕይወታቸው ካለፈው መካከል 21 የሚሆኑት የእስራኤል ጦር ሁለት ሕንጻዎችን ለማውደም የተጠመደው ፈንጅ ከፈነዳ በኋላ መሆኑ ተገልጿል።
እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እንደሚገልጹት ከሆነ የፍልስጤም ተዋጊዎች ከሕንጻዎች ጎን ቆሞ የነበረን ታንክ በሚሳኤል ከመቱ በኋላ ፈንጂዎቹ ፈንድተው ጉዳት አድርሰዋል።
የእስራኤል ጦር ክስተቱን በተመለከተ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አመልክቷል።
የጦሩ ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ የሐማስን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ ከመኖሪያቸው አካባቢ እንዲርቁ ተደርገው የነበሩ እስራኤላውያንን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የተሰማሩ ነበሩ ብለዋል።
ትናንት ሰኞ በሌላ ጥቃት ሦስት የጦሩ አባላት በደቡባዊ ጋዛ መገደላቸውን ቀደም ሲል የእስራኤል መከላከያ አስታውቆ ነበር።
የ24 ወታደሮችን ግድያ ተከትሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ክስተቱን “ጦርነቱ ከተጀመረ ከባዱ ቀን” ሲሉ ገልጸውታል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ “ለጀግኖቻችን ስም ሲባል፤ ለሕይወታችን ስንል ፍጹም ድልን እስክንጎናጸፍ ድረስ መዋጋታችንን አናቆምም” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርጎዝ ደግሞ፣ ይህን ያክል የሟቾች ቁጥር መስማት ከባድ ዜና ነው ብለዋል።
“በመላው የአገሪቱ ሕዝብ ስም ሕይወታቸውን ያጡትን እና የተጎዱትን በጸሎት አስባለሁ” ብለዋል።
መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የሐማስን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ በጋዛ እየተካሄደ ያለው ጦርነት መቀስቀሱ ይታወሳል።
በዛ ድንገተኛ ጥቃት ሐማስ 1ሺህ 200 ሰዎችን ገድሎ 250 የሚሆኑትን ደግሞ አፍኖ መውሰዱ ይታወሳል።
ይህን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ሐማስን እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ በአየር እና በምድር ኃይል የታገዘ ወታደራዊ ዘመቻ በጋዛ ስታካሂድ ቆይታለች።
በዚህም በጋዛ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑ 25ሺህ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በመሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል።
እስራኤል አሁንም ሐማስ ሙሉ በሙሉ እስኪደመሰስ ድረስ ወታደራዊ ዘመቻዬን አጠናክሬ እቀጥላለሁ እያለች ነው።
የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም የደኅንነት ተቋማት እስካሁን ድረስ በእስራኤል ጦር የተገደሉት የሐማስ ተዋጊዎች አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ናቸው ሲሉ ይገምታሉ።
**
ማስታወሻ፡ በዚህ ዜና ላይ የሟቾች ቁጥር ማስተካከያ ተደርጎበታል።












