ቦይንግ ባጋጠመው ችግር ምክንያት 737 ማክስ ምርቶቹ እንደሚዘገዩ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቦይንግ በምርት ወቅት ባጋጠመው ችግር ምክንያት “ከፍተኛ ቁጥር” ያላቸውን ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ለደንበኞቹ ለማቅረብ መዘግየት እንደገጠመው አስታወቀ።
ግዙፉ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ እንዳለው ለ737 ማክስ የኋላኛ ክፍል የሚያስፈልገው ግብዓት አቅራቢ ድርጅት ምርቶቹ የሚጠበቅባቸውን ደረጃ ያሟሉ አይደሉም ብሏል።
የበረራው ዘርፍ ግዙፍ የመንገደኞች አውሮፕላኖች እጥረት ባጋጠመበት በአሁኑ ወቅት፣ የቦይንግ ምርቶች መዘግየት ሌላ ችግር መሆኑ ተነግሯል።
ቦይንግ በምርት ላይ ያጋጠመው ችግር የ737 ማክስ ቤተሰብ በሆኑት የማክስ7፣ የማክስ 8 እና የማክስ 8200 እንዲሁም ፒ-8 ፖሴይዶን የተባሉት የባሕር ላይ ቅኝት የአውሮፕላን ምርቶች አቅርቦት ላይ መስተጓጎልን አስከትሏል።
ቦይንግ የገጠመውን ችግር ለአሜሪካ የበረራ ባለሥልጣን አስታውቆ ሌላ አማራጭ እየፈለገ መሆኑን እና ለደንበኞቹም የአውሮፕላኑ ቀሪ ሥራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ እንደሚያስረክብ ገልጿል።
በዚህም ሳቢያ የቦይንግ የአክሲዮን ገበያ ዋጋ ከአምስት በመቶ በላይ መቀነስን አሳይቷል።
ቀደም ሲል በሌላኛው የቦይንግ ምርት 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ላይ ችግር ማጋጠሙን ተከትሎ በተደረገ ማስተካከ፣ የአሜሪካ የአየር በረራ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን አውሮፕላኑ ወደ ገበያ እንዲመለስ መጋቢት ወር ላይ ፈቅዶ ነበር።
በኮቪድ ምክንያት ተጥሎ የነበረው የጉዞ ክልከላ ከተነሳ በኋላ በዓለም ዙሪያ የአየር ጉዞ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። አየር መንገዶችም ያለውን ፍላጎት ለማሟላት አውሮፕላኖችን ለመግዛት እየተሽቀዳደሙ ይገኛሉ።
ባለፉት ሦስት ወራት ቦይን ለአየር መንገዶች የሸጣቸው አዳዲስ አውሮፕላኖች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ከእነዚህ አብዛኞቹም የ737 ማክስ ሞዴሎች ሲሆኑ ገዢዎቹም ሁለት የአሜሪካ አየር መንገዶች ናቸው።
ቦይንግ በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ አሰቃቂ አደጋ ደርሶ 346 ሰዎች ከሞቱ በኋላ አውሮፕላኑ በዓለም ዙሪያ ከአገልግሎት ውጪ ሆኖው ነበር።
ሁለቱ አደጋዎችን በተመለከተ በተደረጉ ምርመራዎች በአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ላይ በነበረ የዲዛይን ችግር ምክንያት መሆኑ ተደርሶበታል።
ቦይንግ ለአደጋው ሰለባዎች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ካሳ ለመስጠት የተስማማ ቢሆንም፣ ጉዳዩ አሁንም በአሜሪካ ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።
አደጋዎቹን ተከትሎ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከአንድ ዓመት በላይ ከበረራ ውጪ ሆነው በመቆየታቸው የተነሳ ቦይንግ ከፍተኛ ኪሳራ የገጠመው ሲሆን፣ ይህንን ለማስተካከል እና አውሮፕላኖቹን ወደ አየር ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።












