ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናሳ ወደ ጨረቃ የሚልካቸውን የመጀመሪያዎቹን ሴት እና ጥቁር ይፋ አደረገ
የአሜሪካው የጠፈር ድርጅት ናሳ ከ50 ዓመታት በኋላ የሰው ልጅን ወደ ጨረቃ ለመውሰድ በያዘው ዕቅድ መሠረት አራት ጠፈርተኞች ማዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።
ክርስቲና ኮች ለጨረቃ ተልዕኮ የተመደበች የመጀመሪያዋ ሴት ጠፈርተኛ ትሆናለች። ቪክተር ግሎቨር ደግሞ የመጀመሪያው ጥቁር ጠፈርተኛ ይሆናል ተብሏል።
ሁለቱ ጠፈርተኞችን ጨምሮ ሪድ ዊስማን እና ዠርሚ ሃንሰን በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ወይም በ2025 መጀመሪያ ላይ ወደ ጨረቃ ያቀናሉ።
ጠፈርተኞቹ በጨረቃ ላይ ባያርፉም ተልዕኳቸው በቀጣይ ጠፈርተኞች ለሚያደርጉት ጉዞ መንገድ ይከፍታል ተብሏል።
ሦስቱ የአሜሪካ ዜጎች እና ብቸኛው ካናዳዊ በሂዩስተን ቴክሳስ በተካሄደ ስነ ስርዓት ለህዝብ ይፋ ተደርገዋል።
ጠፈርተኞቹ ለጉዞው ራሳቸውን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ስልጠና ይጀምራሉ ተብሏል።
ሴት እና ጥቁር ጠፈርተኛ በመምረጥ ናሳ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጠፈርተኞችን ለመምረጥ የገባው ቃል እንደጠበቀ ተገልጿል። ሁሉም ከዚህ ቀደም ወደ ጨረቃ የተደረጉ ተልዕኮዎች በሙሉ በነጭ ሰዎች የተከናወኑ ናቸው።
ሪድ ዊስማን (47)፡ የዩናይትድ ስቴትስ የባህር ኃይል አብራሪ ሲሆን ለተወሰነ ጊዜ የናሳ የጠፈር ምርምር ቢሮ ኃላፊ ሆኖ አገልግሏል። እአአ በ2015 በቀድሞ የጠፈር ተልዕኮ ወደ ዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ ተጉዟል።
ቪክተር ግሎቨር (46)፡ ናሳን የተቀላቀለው እአአ በ2013 ሲሆን የመጀመሪያ የጠፈር ተልዕኮውን በ2020 አከናውኗል። ለስድስት ወራት በህዋ ጣቢያ መቆት የቻለ የመጀመሪያው ጥቁር ሆኗል።
ክርስቲና ኮች (44): በሙያዋ የኤሌክትሪክ መሐንዲስ ናት። ለ328 ቀናት በመቆት የሴቶችን ክብረ ወሰብ ሰብራለች። ከናሳ ጠፈርተኛዋ ጄሲካ ሜየር ጋር በ2019 በሴቶች ብቻ በተደረገ የጠፈር ጉዞ ላይ ተሳትፋለች።
ዠርሚ ሃንሰን (47)፡ የካናዳ የጠፈር ኤጀንሲን ከመቀላቀሉ በፊት በሮያል ካናዳ አየር ሃይል የተዋጊ ጄት አብራሪ ነበር። ወደ ጠፈር እስካሁን አልተላከም።
"የአርተሚስ-2 ጠፈርተኖች እኛን ወደ ጨረቃ ለመውሰድ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚደክሙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ይወክላሉ” ሲሉ የናሳ አስተዳዳሪ ቢል ኔልሰን ተናግረዋል።
"የናሳ ጠፈርተኞች ሪድ ዊስማን፣ ቪክተር ግሎቨር እና ክሪስቲና ሃሞክ ኮች እና የሲኤስኤ ጠፈር ተመራማሪው ዠርሚ ሃንሰን የራሳቸው ታሪክ አሏቸው። በአንድነት ግን መግለጫችንን ይወክላሉ። ለአዲሱ ትውልድ ኮከብ ጠፈርተኞች እና ህልም ላላቸው አዲስ የምርምር ዘመን እየፈጠርን ነው” ብለዋል።
ወስማን የጉዞው አዛዥ ይሆናል። ግሎቨር የእሱ አብራሪ ሲሆን ኮች እና ሃንሰን ደግሞ ለ“ተልዕኮው” ድጋፍ ሰጪዎች ይሆናሉ።
አራቱ በ1968 በአፖሎ 8 የተካሄደውን ተልዕኮ ይደግማሉ። ይህም የሰው ልጅ ወደ ጨረቃ የደረሰበት መጀመሪያው የጠፈር በረራ ነበር።
ሰራተኞቹ ቤታችን ፕላኔታችን ከጨረቃ አድማስ ጀርባ መውጣቷን የሚያሳየውን ታዋቂውን "Earthrise" ምስል አነሱ።
ዋነኛው ልዩነት ናሳ በአርተሚስ ፕሮግራሙ የ 21 ኛው ክፍለ ዘመን ቴክኖሎጂ መጠቀሙ ነው። በግሪክ አፈ ታሪክ መሠረት አርተሚስ የአፖሎ መንታ እህት ነበረች።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ድርጅቱ አዲሱን የጨረቃ ሮኬቱን የስፔስ ላውንች ሲስተም እና ተያያዥነት ያላቸውን የሰራተኞች ማጓጓዣ ኦሪዮንን ሞክሯል።
በዚህ የአርተሚስ-1 ተልዕኮ ምድርን በመልቀቅ ያለምንም ጠፈርተኛ በጨረቃ ዙሪያ ለ25 ቀናት ጉብኝት አድርጓል። በዚህም መሐንዲሶች የመሣሪያውን ዝግጁነት እንዲገመግሙ አስችሏቸዋል።
ይፋ የተደረጉት ጠፈርተኞች ኦሪዮንን በመጠቀም በአርተሚስ-2 ወደ ጨረቃ የደርሶ መልስ ጉዞ ያደርጋሉ። ይህም 10 ቀናትን ያህል ሊወስድ ይችላል።
ለመጨረሻ ጊዜ የሰው ልጅ ወደ ጠፈር በረራ ያደረገው በ1972 በአፖሎ 17 ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ጠፈር ላይ ያረፈው ደግሞ በአፖሎ 11 በ1969 ነበር።
አርተሚስ-3 ወደ ጅራ ለመግባት ቢያንስ ከአርተሚስ-2 በኋላ እስከ 12 ወራት ድረስ ይወስድበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ናሳ ጠፈርተኞችን ወደ ጨረቃ እንዲራመዱ የሚያስችል ስርዓት እስካሁን የለውም። ይህ በቢሊየነሩ ኢሎን መስክ ስፔስ ኤክስ ኩባንያ እየተዘጋጀ ይገኛል።
ስታርሺፕ ተብሎ የሚጠራው ተሽከርካሪው በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት የበረራ ሙከራ ይጀምራል።
"በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አጋጣሚ ማክበር አለብን፤ ምክንያቱም አርተሚስ-2 ከጨረቃ ደርሶ መልስ ተልዕኮም በላይ ነው። ሰዎችን ወደ ጨረቃ ወለል ከመላካችን በፊት መከናወን ያለበት ተልዕኮ ነው። ወደ ማርስ ለሚደረገው ጉዞ ቀጣዩ ደረጃ ነው ሲል ቪክተር ግሎቨር በሂዩስተን ሥነ ሥርዓት ወቅት ተናግሯል።
ክርስቲና ኮች በበኩሏ"ደስተኛ ናችሁ? ይህንን ጠየቅሁት ደስታዎን፣ ምኞቶችዎንና ህልሞችዎን ከእኛ ጋር በዚህ ተልዕኮ ይዘን ስልምጓዝ ነው” ብላለች።
ቫኔሳ ዋይሽ የተልዕኮው የቁጥጥር ጣቢያ በሆነው የናሳ ጆንሰን የጠፈር የበረራ ማዕከል ዳይሬክተር ናት።
"[ከአርተሚስ-2] ጠፈርተኞች መካከል የመጀመሪያዋ ሴት፣ የመጀመሪያው ጥቁር እና የመጀመሪያው ካናዳዊ በጨረቃ ተልዕኮ ላይ ይገኛሉ። አራቱም የጠፈር ተመራማሪዎች የሁሉንም ጥቅም ለማግኘት በመሞከር የሰው ልጅ ይወክላሉ” ብላለች።