ትራምፕ በጠሩት ሰልፍ ደጋፊዎቻቸው ለመሳተፍ ሰግተዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶናልድ ትራምፕ ሊቀርብባቸው የሚችለውን ክስ ደጋፊዎቻቸው እንዲቃወሙ ጥሪ አቀርበዋል።
ፖሊስም ሊፈጠር የሚችለውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር በአሜሪካ ታላላቅ ከተሞች ውስጥ ዝግጅት እያደረገ ነው።
በተጨማሪም ዶናልድ ትራምፕ ከሚተማመኑባቸው ደጋፊዎች መካከል አንዳንዶቹ ቤት መቆየትን መርጠዋል።
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የትራምፕ ደጋፊዎች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ምርመራ መደረግ መጀመሩ ነው።
በማኅራዊ ሚዲያ የትስስር ገጾች፣ በመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች እና ትራምፕ በባለቤትነት በያዙት ትሩዝ ሶሻል ላይ የተለያዩ አሉባልታዎች እየተሰራጩ ነው።
በእነዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጾች በኩል ወደ ሁከት የሚመሩ መልዕክቶች እየተላለፉ ነው።
በርካታ የቀድሞ እና ጠንካራ የትራሞፕ ደጋፊዎች በፈረንጆቹ 2021 ጥር ወር የተቀሰቀሰውን የካፒቶል ሁከት መነሻ ትራምፕ ሳይሆኑ የፌዴራል ተቋማት እና ግራ ዘመምም ፖለቲከኞች እንደቀሰቀሱት ያምናሉ።
ደጋፊዎቹ ለዚህም ማሰረጃ ይሆነናል የሚሉት በዚያን ቀን በምስጢር የተያዘ ምንጭ በፍርድ ቤት ይፋ ያወጠው ሰነድ ነው።
ሆኖም የፌዴራል ባለሥልጣናት ሁከትን ቀስቅሰዋል ለማለት የሚያስችል መረጃ የለም። በተቃራኒው ከሁከቱ ጋር ግንኙነት እንደላቸው የተጠረጠሩ ከ 1 ሺህ በላይ የትራምፕ ደጋፊዎች እንደሆኑ የተገመቱ ሰዎች ታስረዋል።
ስለዚህ ትራምፕ ሊታሰሩ እንደሚችሉ ከታወቀ በኋላ የዚያን ጊዜው አይነት ሁከት እንዳይቀሰቀስ ተሰግቷል።
ወደ ሁከት የተቀየረውን የካፒቶል ተቃውሞ የመራው የቀኝ አክራሪ አክቲቪስት ከትራምፕ እስር ጋር በተያያዘ ለተቃውሞ የመውጣት ዕቅድ እንደሌለው ተናግሯል። ሌላኛው የሴራ ፖለቲካ ተንታኝ አሌክስ ጆንስም በቤቱ ይቆያል።
ለትራምፕ ባላቸው ታማኝነት የሚታወቁት የጆርጂያ የሪፐብሊካን ተወካይ ማርጆሪ ታይለር ግሪንም ተመሳሳይ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ሌሎችም መሰል ምልዕክቶች የትራምፕ ደጋፊዎች በሚጠቀሙበት የማኅበራዊ ትስስር ገጾች እየተሰራጩ ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት በአሜሪካ ምክር ቤት ሕንጻ ካፒቶል ሂል ላይ ሁከትን ያስከተለውን ተቃውሞ ከጠሩበት ሁኔታ በተቃራኒ ትራምፕ አንድ የተለየ የመሰባሰቢያ ቦታ እና ጊዜ ሊጠሩት ለሚችሉት ተቃውሞ ያሉት ነገር የለም።
ሆኖም በትራምፕ ተቀናቃኞች ላይ ጥቃት ሊደርስ ይችላል የሚሉ ንግግሮች ከፍ ባለ መጠን መደመጥ ጀምረዋል።
አድቫንስ ዴሞክራሲ የተባለ እና ገለልተኛ የምርምር ተቋም ትራምፕ ባለፈው ቅዳሜ በራሳቸው ማኅበራዊ ሚዲያ ሊታሰሩ እንደሚችሉ ገልጸው “ተቃወሙ፣ አገራችንን መልሷት” ሲሉ መልዕክት ካጋሩ በኋላ በዚያው ማኅበራዊ ሚዲያ ለጥቃት የሚያነሳሱ መልዕክቶች መኖራቸውን ገልጿል።
የሕግ አስከባሪ ተቋማት እንዲህ አይነቶቹን ዛቻዎችን እና ተቃውሞች በከፍተኛ ክብደት ይመለከቱታል።
የኒውዮርክ ፖሊስ ትራምፕ እንዲታሰሩ ውሳኔ ሊያሳልፍ ይችላል በተባለው ፍርድ ቤት አቅራቢያ ያለውን የፀጥታ ኃይል አጠናክረዋል።
በሎስ አንጀለስ ፖሊስ ከፌደራል ሕንጻዎች ውጪ የትራምፕ ደጋፊዎች ሊያነሱ የሚችሉትን አመጽ ለመቆጣጠር መዘጋጀታቸው ተዘግቧል።
በዋሽንግተን ፖሊስ የትራፕ ደጋፊዎች ለተቃውሞ መዘጋጀታቸውን የሚገልጽ የተለየ መረጃ ባይደርሰውም የሲቪል የፀጥታ መኮንኖች በተጠንቀቅ ላይ ናቸው።
ቅዳሜ ትራምፕ በዋኮ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ አቅደዋል።












