ሐማስ የጦር አዛዡ መሃመድ ዴይፍ መሞቱን አረጋገጠ

የጦሩ አዛዥ መሃመድ ዴይፍ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሐማስ የጦር አዛዡ መሃመድ ዴይፍ መገደሉን አረጋገጠ።

የእስራኤል ጦር ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ዴይፍ መገደሉን ቢያስታውቅም ሐማስ እስካሁን ድረስ ሞቱን አላረጋገጠም ነበር።

እስራኤል ዴይፍ ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ 1 ሺህ 200 ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት ካቀነባበሩት መካከል አንዱ ነው ብላለች።

ዴይፍ በእስራኤል ጦር ጥቅምት ወር ላይ የተገደለው የጋዛ ግዛት የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ምክትል ተደርጎ በሰፊው ይታይ ነበር።

የአለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት እንዲሁም ከሐማስ በኩል የእስር ማዛዣ ከወጣባቸው መካከል አንዱ ዴይፍ ነው።

ዴይፍ የሐማስ ተዋጊዎች ከጋዛ ወደ እስራኤል እንዲገቡ ያስቻላቸውን ዋሻዎች በመገንባት ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ይታወቃል።

በተጨማሪም የሐማስ መለያ የሆነውን የቃሳም ሮኬትን ንድፍ በመስራትም ዕውቅና ተሰጥቶታል።

ሐማስ፣ ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ በተጨማሪ ምክትል ወታደራዊ አዛዡ ማርዋን ኢሳ መሞቱን ገልጿል። አሜሪካ ኢሳ መሞቱን ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ አስታውቃ ነበር።

ኢሳ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ምክትል አዛዥ ሲሆን እስራኤል በጥብቅ ከምትፈልጋቸው አመራሮች አንዱ ነበር። ሐማስን በአሸባሪነት የፈረጀው የአውሮፓ ህብረትን ኢሳን ከመስከረሙ ጥቃት ጋር በቀጥታ አያይዞታል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ47,460 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

በእስራኤል እና በጋዛ የተደረሰው የጋዛው የመጀመሪያ ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት እሁድ፣ ጥር 11/ 2017 ዓ.ም ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ 15 ታጋቾች ተለቀዋል።

እስራኤል በበኩሏ በእስር ቤቷ የያዘቻቸውን ያለ ክስ የታሰሩ በርካታ ታዳጊዎችን ጨምሮ 400 ፍልስጤማውያንን ለቃለች። አብዛኞቹም እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክን ጨምሮ፣ ወደ ምስራቃዊ ኢየሩሳሌምና ጋዛ ተመልሰዋል። ከፍተኛ ጥፋት ፈጽመዋል የተባሉ 70 ሰዎች ከአገር መባረራቸው ተገልጿል።