“ከ80 ዓመት በኋላ ድጋሚ ታንክ የላከችብን ጀርመን የእጇን ታገኛለች” ፑቲን

ቪላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፑቲን የመታሰቢያ ጉንጉን አበባ ሲያስቀምጡ
ታትሟል

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ጀርመን ከ80 ዓመት በኋላ ድጋሚ ታንክ መላኳን ጠቅሰው አጸፋው ከባድ እንደሚሆን አስጠነቀቁ።

ፑቲን ዛቻውን የሰነዘሩት የ2ኛው የዓለም ⶏርነት የስታሊንግራድ ፍልሚያ 80ኛ ዓመት በተዘከረበት መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ፑቲን በዩክሬን የሚደረገው ፍልሚያ አገራቸው ከጀርመን ናዚ ጋር ካደረገችው ጦርነት ጋር አዛምደውታል።

ጀርመን ከዩክሬን ጎን መቆሟና ታንክ በኛ ላይ መላኳ “ታሪክ ራሱን እንደሚደግም ማሳያ ነው” ብለዋል ፑቲን።

“በእውነቱ ይህ የማይታመን ቢሆንም ጥሬ ሐቅ ነው። በታሪክ ለ2ኛ ጊዜ በጀርመን ሊዮፓርድ ታንክ ዛቻ ደርሶብናል” ሲሉ የጀርመን ተሳትፎ እንዳበሳጫቸው ፑቲን በንግግራቸው አንጸባርቀዋል።

ጀርመን ዩክሬንን በእጅጉ በወታደራዊ ኃይል እያገዙ ካሉ ምዕራብ አገራት አንዷ ናት።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ የፈጸመችው የዛሬ ዓመት ነበር።

ወረራውን ተከትሎ በርካታ ምዕራብ አገራት የሩሲያን ጥቃት ለመመከት ያስችል ዘንድ ለዩክሬን ከፍተኛ የገንዘብ፣ የትጥቅና የጦር መሣሪያ እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ።

ሩሲያ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ አጠናቅቃለሁ ብላ የነበረ ቢሆንም ነገሩ እንዳሰበችው ቀላል አልሆነላትም።

ፑቲን ቀድሞ ስታሊንግራን አሁን ቮልጎግራድ ተብላ በምትታወቀው ከተማ ባደረጉት የ80 ዓመት ጦርነት መታሰቢያ ንግግር ምዕራባዊያን ሩሲያን በመዳፈራቸው የእጃቸውን እንደሚያገኙ ዝተዋል።

የ70 ዓመቱ ፑቲን “ራሺያን በጦር ሜዳ እንደሚያሸንፉ የሚያስቡ ዘመናዊ ጦርነት ምን ያህል የተለየ እንደሆነ የማይረዱ ናቸው” ብለዋል።

ጨምረውም፣ “እኛ ታንኮቻችንን ወደነርሱ ድንበር አንልክም፤ ነገር ግን ለጥቃታቸው አጸፋውን በሚገባ መንገድ እንመልሳለን። ይህን ሁሉም ሰው መረዳት ይገባዋል” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፐስኮቭ ፑቲን ይህን ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ እንዲያብራሩ ተጠይቀው አልመለሱም። ነገር ግን ምዕራባዊያን ዘመናዊ ጦር መሣሪዎችን ወደ ዩክሬን መላካቸው ሩሲያ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችላት በደፈናው ጠቁመዋል።

የ2ኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ያገኘበት የስታሊንግራድ ጦርነት የዛሬ 80 ዓመት 91ሺህ ጀርመናዊያን የተማረኩበት ነበር።

በዚህ ጦርነት ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወታደሮች እንደሞቱ ይነገራል።

ቮልጎግራድ ለዚህ መታሰቢያ ሲባል ለጊዜው ስታሊንግራድ ተብላ ስትጠራ ነበር በዕለቱ። ከዚህም ሌላ ለአምባገነኑ ጆሴፍ ስታሊን የተሠራ መታሰቢያ ሐውልትም ተመርቋል።

ሶቭየት ኅብረትን የመሯት ጆሴፍ ስታሊን ከ1924 እስከ ሞታቸው 1953 ዓ/ም ነበር።

ጆሴፍ ስታሊን በዘመናቸው በዩክሬን ረሀብ እንዲከሰት አድርገዋል ተብለው ይወቀሳሉ። ዩክሬናዊያን ሆሎዶሞር ብለው በሚጠሩት በዚህ ሰው ሰራሽ ረሀብ 5 ሚሊዯን ዜጎች እንዲሞቱ ሆነዋል።

በዚህ ወር በቡልጋሪያ በተደረገ ጉባኤ ይህ የስታሊን ተግባር የዘር ማጥፋት ተብሎ ዕውቅና አግኝቷል።

ፑቲን በዚህ መታሰቢያ ላይ ባደረጉት ንግግር ናዚዝም ከ80 ዓመት በኋላ ዳግም መቀስቀሱን ጠቅሰዋል።

“ጀርመን ታንክ ብትልክብንም ሞስኮ ምን ማድረግ እንዳለባት ታውቃለች” ብለዋል።

በርሊን ለዩክሬን 14 እጅግ ዘመናዊ የሚባሉ ሊዮፓርድ-2 ታንኮችን ለመለገስ መወሰኗን ተከትሎ አንድ የሩሲያ ኢንዱስትሪ እነኚህ ታንኮች ላይ ጥቃት ለሚያደርስ የሩሲያ ወታደር አምስት ሚሊዮን ሩብልስ እሸልማለሁ ብሏል።

በዚህ የመታሰቢያ መርሐ ግብር ፒቲንን ያጀቡት የቮልጎግራድ ገዢ አንድሬይ ቡቻሮቭ ከጥር 24 ጀምሮ ከፑቲን ጋር እስኪታዩ ድረስ ተሰውረው ነበር። ምናልባት ከፑቲን በቅርብ ርቀት ለመቆም ራሳቸውን ለቀናት ማግለል ስለነበረባቸው ነው የጠፉት ተብሎ ተገምቷል።

ከፑቲን ጋር በቅርብ ርቀት የሚቆሙ ሰዎች በቅድሚያ የጤና ምርመራ የሚደረግላቸው ሲሆን ከሁለት ሳምንት ቀደም ብሎም ራሳቸውን ሆቴል ውስጥ እንዲያገሉ ይደረጋል።