እስራኤል እና ሱዳን የሰላም ስምምነት በዋሽንግተን ዲሲ ሊፈራረሙ ነው

ሱዳን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

እስራኤል እና ሱዳን ከጥቂት ወራት በኋላ በዋሽንግተን ዲሲ “ታሪካዊ የሰላም ስምምነት” እንደሚፈራረሙ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነቱን በመፈራረም ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የተስማሙት በካርቱም ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኤሊ ኮሃን ወደ ሱዳን ተጉዘው ከአብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ጋር ከተገናኙ በኋላ ሁለቱ አገራት ፊርማቸውን የሚያኖሩበት ሰነድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ሱዳን ከሁለት ዓመታት በፊት ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ብትስማማም ስምምነት ግን እስካሁን ሳይፈረም ቆይቷል።

በአሜሪካ አደራዳሪነት የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ባህሬን እና ሞሮኮ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከእስራኤል ጋር ግንኙነታቸውን ያሻሻሉ የአረብ አገራት ናቸው።

የአረብ-እስራኤል ግጭትን ምክንያት በማድረግ በርካታ የአረብ ሊግ አገራት ለእስራኤል እውቅና ከመስጠት ተቆጥበው ነበር።

ግብጽ እአአ 1979 ላይ ለእስራኤል እውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ አረብ አገር ሆና ነበር። እአአ 1994 ላይ ደግሞ ጆርዳን ለእስራኤል እውቅና በመስጠት ሁለተኛዋ አገር ሆናለች።

የሱዳን እና የእስራኤል ሰምምነትን በተመለከተ ሌተናንት-ጀነራል ቡርሃን እና የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኮሃን በሁለቱ አገራት መካከል “ውጤታማ የሆነ ግንኙነት መመሥረት በሚቻልበት ሁኔታ ተመካክረዋል” ብሏል የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።

ካርቱም ግን የሰላም ስምምነቱ እንደሚፈርም እስካሁን ያለችው ነገር የለም።

በርካታ የአረብ አገራት ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል መስማማታቸው ፍልስጤማውያንን ያበሳጨ ጉዳይ ሆኗል።

ለዓመታት የአረብ አገራት ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት በመድረስ ለአገሪቱ እውቅና የምንሰጠው ከፍልስጤም ጋር ያላትን አለመግባባት በንግግር ፈትታ፣ በኃይል ከያዘቻቸው ቦታዎች ለቅቃ እና ፍልስጤም ምሥራቅ እየሩሳሌም መዲናዋ ሆና እንደ አገር ስትመሠረት ነው የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀምጡ ነበር።

እስካሁን ድረስ ለእስራኤል እውቅና ከማይሰጡ አገራት መካከል ሳኡዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ኢራቅ እና ሶሪያ ይጠቀሳሉ።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከካርቱም ጉዟቸው ሲመለሱ ወደ ሱዳን የተጓዙት “በአሜሪካ ፍቃድ” መሆኑን ተናግረዋል።

ጉብኝቱ “ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ካላት የአረብ እና ሙስሊም አገር ጋር ለሚደረሰው የሰላም ስምምነት መሠረት የጣለ ነው” ብለዋል ኮሃን።

ሚንስትሩ በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረሰው የሰላም ስምምነት ለእስራኤል እና ለቀጠናው ሰላም እና መረጋጋትን የሚያመጣ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

ሁለቱ አገራት የሰላም ሰምምነቱን የሚፈራረሙት በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ላይ የወጣው ጦር ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር ሲያስክረብ ይሆናል ተብሏል።