በዩኬ ቀኝ አክራሪዎች ያደረጓቸው ሰልፎች ወደ ብጥብጥ ተቀይረው ከ90 በላይ ሰዎች ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቅዳሜ ዕለት በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ ከተሞች ቀኝ አክራሪዎች ሁከትና ብጥብጥ መቀስቀሳቸውን ተከትከሎ ከ90 በላይ ሰዎች ታስሩ።
ሃል፣ ሊቨርፑል፣ ብሪስቶል፣ ማንቸስተር፣ ስቶክ-ኦን-ትሬንት፣ ብላክፑል እና ቤልፋስትን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ጠርሙሶች ተወርውረዋል፣ ሱቆች ተዘርፈዋል እንዲሁም የፖሊስ መኮንኖች ጥቃት ደርሶባቸዋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር "ጥላቻን ለመዝራት" በሚሞክሩ "አክራሪዎች" ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ለፖሊስ ሃይሎች መንግስት ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ሰኞ ዕለት በሳውዝፖርት መርሲሳይድ በቴይለር ስዊፍት የዳንስ ድግስ ላይ ሦስት ወጣት ልጃገረዶች ከተገደሉ በኋላ ውጥረት ነግሷል።
በሊቨርፑል ጠርሙሶች እና እሳት በፖሊሶች ላይ ተወርውረዋል። አንድ ፖሊስ በተወረወረበት ወንበር ጭንቅላቱን ተመትቶ ሲጎዳ፣ ሌላኛው ደግሞ ከሞተር ሳይክሉ ላይ ተመትቶ ወድቋል።
ሊቨርፑል ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፀረ ፋሺስት ተቃዋሚዎች አንድነት እና መቻቻልን በመስበክ "ስደተኞች እዚህ ይምጡ" እና "የናዚ ተላላኪዎች ከመንገዳችን ይውጡ" ብለዋል።
ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ስደተኞችን ከሚቃወሙ እና የተወሰኑት ጸረ እስላም ያላቸውን ስድቦችን ሲሰነዝሩ ከነበሩ ሰልፈኞች ጋር ለመጋፈጥ ወደ ከተማዋ ወንዝ ዳርቻ አቅንተዋል።
ፖሊስ ሁለቱን ወገኖች መለያየት ባለመቻሉ ተጨማሪ ሃይል እንዲደርስ ጥሪ ቀርቦ ነበር።
ብጥብጡ እስከ ቅዳሜ እኩለ ለሊት ድረስ የቀጠለ ሲሆን በፖሊስ መኮንኖች ላይ ርችቶች ተተኩሰዋል።
በከተማዋ የሚገኝ ቤተመጽህፍት መቃጠሉን እና ሁከት ፈጣሪዎቹ የእሳት አደጋ ተከላካዮች እሳቱን እንዳያጠፉት ለማድረግ ሞክረዋል ሲል የመርሲሳይድ ፖሊስ አስታውቋል።
ሱቆች መሰባበራቸውን እና በርካታ ቆሻሻ መጣያዎች መቃጠላቸውንም አክሏል።
ረዳት ዋና ኮንስታብል ጄኒ ሲምስ “ስርዓተ አልበኝነት፣ ብጥብጥ እና ውድመት መርሲሳይድ ውስጥ ቦታ የላቸውም” ሲሉ ገልጸዋል።
“በዚህ ተግባር የተካፈሉ ሰዎች በራሳቸውና በዚች ከተማ ላይ እፍረት ከማምጣት ውጪ ምንም አያስገኙም" ብለዋል።
ባለፈው ቅዳሜ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬየር ስታርመር “ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እና ያየነው ሁከትና ብጥብጥ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው” ስለማለታቸው ተገልጿል።
አክለውም “ለማንኛውም ዓይነት ሁከት ምክንያት የለም። ከተሞቻችንን ከአደጋ ለመጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ መንግስት ፖሊስን ይደግፋል” ብለዋል።
ቅዳሜ ዕለት የሀገር ውስጥ ሚኒስትሯ “ተቀባይነት በሌለው ረብሻ” ውስጥ የሚሳተፍ ማንኛውም ሰው እስራት እና የጉዞ እገዳ እንደሚጠብቀው አስጠንቅቀው “በቂ” የእስር ቦታዎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
ኢቬት ኩፐር አከክለውም “የወንጀል ጥቃት እና ስርዓት አልበኝነት በብሪታንያ ጎዳናዎች ላይ ምንም ቦታ የላቸውም" ብለዋል።
ፖሊስ ”በዘራፊዎች ላይ ለሚወስደው እርምጃ የመንግስት ሙሉ ድጋፍ አለው" ሲሉ አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, PA
በብሪስቶል ተቃዋሚዎች እና እነሱን በሚቃወሙ መከላከል ፍጥጫ ተፈጥሮ ነበር።
አንደኛው ወገን “እንግሊዝ ወይም ሞት” እና “አገራችን እንድትመለስልን እንፈልጋለን” ሲል ሌላኛው ወገን ደግሞ “ስደተኞች በደስታ እንቀበላለን” ሲሉ ተሰምቷል።
የአቨን እና ሱመርሴት ፖሊስ በከተማዋ ውስጥ 14 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
በማንቸስተር ከፖሊስ ጋር ፍጥጫ የነበረ ሲሆን ቢያንስ ሁለት ሰዎች ታስረዋል።
በቤልፋስት ከመስጊድ ውጭ የነበሩ ተቃዋሚዎች በመገናኛ ብዙሃን አባላት ላይ እቃ ሲወረውሩ የነበረ ሲሆን ቀደም ብሎ ደግሞ የካፌ መስኮቶች ተሰባብረዋል። በከተማዋ ሁለት ሰዎች ታስረዋል።
በሁል ተቃዋሚዎች ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚኖሩበትን ሆቴል መስኮት ሰብረው ጠርሙሶች እና እንቁላሎች በፖሊስ ላይ ወርውረዋል።
የሃምበርሳይድ ፖሊስ ሶስት የፖሊስ አባላት መቁሰላቸውን እና 20 ሰዎች በከተማው መሀል በተፈጠረ አለመረጋጋት በቁጥጥር ስመዋላቸውን ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Justin Tallis / AFP
የላንካሻየር ፖሊስ ከ20 በላይ ሰዎችን ማሰሩን አስታውቋል።
በስቶክ-ኦን-ትሬንት ጡቦች በፖሊሶች ላይ ተወርውረዋል።የስታፎርድሻየር ፖሊስ 10 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና ሦስት መኮንኖች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።
የሌስተርሻየር ፖሊስ ደግሞ በሌስተር ከተማ መሃል ሁለት ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል። የምዕራብ ዮርክሻየር ፖሊስ ደግሞ በሊድስ ሄሮው በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ አንድ ሰው በቁጥጥር ስር ቢያውልም ተቃውሞ ተጨማሪ ችግር አላስከተለም ብሏል።
በዩናይትድ ኪንግደም የተካሄዱት ሰልፎች በሙሉ ወደ ብጥብጥ አልተሸጋገሩም። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ተቃዋሚዎች እስከ ምሽት ቆይተው ተበትነዋል።
የቅዳሜው ተቃውሞ አርብ እለት በሰንደርላንድ የተካሄደውን ብጥብጥ ተከትሎ የመጣ ሲሆን አራት ፖሊሶች ሆስፒታል ገብተዋል።












