በናይጄሪያ የጀልባ አደጋ ቢያንስ 150 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

ታትሟል

በናይጄሪያ በሚገኘው ኒጀር ወንዝ ላይ በደረሰው የጀልባ አደጋ ቢያንስ 150 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

በናይጄሪያ ደቡብ ምዕራብ ግዛት የሚገኘው ኩዋራ ግዛት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማግኘት ሙከራ እየተደረገ እንደሆነ ገልጿል።

እስካሁን 53 ሰዎችን በሕይወት ማትረፍ ተችሏል።

በደረሰው አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው አምስት ማኅበረሰቦች አሁንም ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ እንደገቡ ነው።

ጀልባውን የተሳፈሩት 300 ሰዎች ነበሩ።

ሠርግ ለመታደም ወደ አጎራባች ከተማ ሄደው እየተመለሱ ሳለ ነው አደጋው የደረሰው።

እስካሁን ካልተገኙ መካከል አባትና አራት ልጆቹ ይገኙበታል።

የኩዋራ ግዛት አገረ ገዢ አብዱልራሐም አብዱልራዛቅ ከሰኞ ጀምሮ ሰዎችን ለማዳን እየተሞከረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ደብዛቸው የጠፉ ሰዎች ከዚህ በኋላ በሕይወት ይገኛሉ የሚለው ተስፋ ግን እየደበዘዘ መጥቷል።

ፓቲጊ የተባለው ግዛት ባህላዊ መሪ ኢብራሒም ዑመር ቦሎጊ እንደተናገሩት ወንዙ ላይ የተነሳው ወጀብ ጀልባውን መገልበጥ ችሏል።

ጀልባው ከመስመጡ በፊት ከዛፍ ጋር እንደተጋጨና ወደ ወንዙ ውስጥ እንደሰጠመም ገልጸዋል።

በኒጀር ወንዝ የሚጓዙ ሰዎች ከዚህ ቀደምም ለአደጋ ተጋልጠዋል።

የየብስ መንገድ አመቺ ሳይሆን ሲቀር በፍጥነት ለመጓጓዝ ወንዙን ይጠቀማሉ።

ጀልባው ሰኞ ዕለት ከኒጀር ግዛት ወደ ኩዋራ እየተጓዘ ሳለ ነው አደጋው የገጠመው።

የኩዋራ አገረ ገዢ በአደጋው ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

ባለፈው ወር ሌላ ጀልባ ሰጥሞ 14 ሰዎች ሞተዋል።