ታይላንድ፡ በትምህርት ቤቷ ከደረሰው ጥቃት የተረፈችው ብቸኛዋ የሦስት ዓመት ልጅ  

ታትሟል

የሦስት ዓመቷ ኤሚ በሰሜን ታይላንድ በሚገኝ የሕጻናት ማቆያ ውስጥ ከምትወዳት ጓደኛዋ አጠገብ በተኛችበት አጋጣሚ ነው ሽጉጥና ቢላዋ የታጠቀ ጥቃት አድራሽ ወደ ክፍሉ የገባው።

በክፍሉ 11 ህጻናት ይማሩበታል። ሁሉም ዕድሜያቸው ሦስት ዓመት ገደማ ነው። በመሳል እና በመጻፍ ተጠምደው ነበር የቆዩት። አራት ሰዓት ገደማ መምህራን በፈገግታ የተሞሉ የደስተኛ ልጆቻቸውን ፎቶ ለወላጆቻቸው ልከዋል።

ስድስት ሰዓት ገደማ ሁሉም ልጆች የእረፍት ሰዓታቸውን በመተኛት እያሳለፉ ነበር። በዚህ ወቅት ነው የቀድሞ ፖሊስ አባል የነበረው ፓንያ ካምራብ ወደ ሕንጻው የገባው።

 በመጀመሪያ የስምንት ወር ነፍሰ ጡር የሆነችውን አስተማሪን ጨምሮ ሠራተኞችን በጥይት መታቸው። ቀጥሎ ወደ ሦስቱ የመዋዕለ ሕፃናት ክፍሎች መግባቱን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

ሁሉንም የኤሚ ጓደኞች በተኙበት ገደላቸው።

እሷ እንዴት እንደተረፈች ምንም አልታወቀም። ነቅታ ከክፍል ጓደኞቿ አስከሬን አጠገብ እጥፍጥፍ ብላ ተገኘች።

የ59 ዓመቷ አያቷ ሶምሳክ ስሪቶንግ አእንደሚሉት “ስትነቃ ምን እንደተፈጠረ አታውቅም ነበር።”

"ጓደኞቿ አሁንም የተኙ መስሏት ነበር። አንድ ፖሊስ ፊቷን በጨርቅ ሸፍኖ ከከፍሉ አስወጣት።“

የነፍስ አድን ሠራተኞች ከአስፈሪው ሁኔታ ለመጠበቅ ኤሚን ወደ ሁለተኛ ፎቅ ወሰዷት። ሌሎችን በህይወት እናገኝ ይሆን በሚል ተስፋ ሌሎቹን ሁለት ክፍሎች መፈተሽ ጀመሩ።

ሐሙስ ዕለት በኖንግ ቡአ ላምፉ ከተፈጸመው እልቂት በህይወት የመትረፍ የቻለች ብቸኛ ልጅ ሆነች። የጥቃት አድራሹን ሚስት እና የእንጀራ ልጅን ጨምሮ በአጠቃላይ 37 ሰዎች ተገድለዋል።

ከሟቾቹ ውስጥ 24ቱ ህጻናት ናቸው።

ሶምሳክ "በመትረፏ ምስጋና አቀርባለሁ። መጀመሪያ እንዳየዃት አጥብቄ ያዝኳት" ብለዋል

የ35 ዓመቷ ፓኖምፓይ ስሪቶንግ የኤሚ እናት ናት። በሳምንቱ የሥራ ቀናት ባንኮክ ትሠራለች። በማዕከሉ ውስጥ ያሉት ሁሉም ልጆች እንደሞቱ ተነግሯት የነበረ ሲሆን  ልጇ አሁንም በህይወት እንዳለች ለማመን ጊዜ ወስዶባታል። 

"ከኤሚ ጋር የቪዲዮ ጥሪ ካደረግኩ በኋላ ነው እፎይ ያልኩት” ትላለች።

ይህች ትንሽ ከተማ በሃዘን በተሰበሩ ቤተሰቦች ተሞልታለች። በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት የኤሚ አያቶች ምን እንደሚነግሯት ግራ ተጋብተው ነበር።

በአትክልት ስፍራ ስትጫወት ቀስ ብለን እናወራለን። ታቺንግ የተባለችው የቅርብ ጓደኛዋን የሦስት ዓመቷን ፓታራውትን ደጋግማ ትጠይቃለች።

ሁልጊዜም እግሮቻቸው እንደተነካኩ አብረው ይተኛሉ።  ማዕከሉን ስለምትወደው ልክ እንደ አስተማሪዎችዋ መሆን ትፈልጋለች።

"በመጨረሻም ሴት አያቷ የትምህርት ቤት ጓደኞቿና መምህሯ ሁሉም እንደሞቱ እና የሕፃናት ማቆያ ማዕከሉ እንደተዘጋ ነገሯት" ትላለች እናቷ።

"እሷ በየቀኑ ትምህርት ቤት መሄድ ትፈልጋለች። ትምህርት ቤቱ እንደተዘጋ ደጋግመን እንነግራታለን። የሞትን ጽንሰ-ሃሳብ ለመረዳት በጣም ትንሽ ነች።"

የቡድሃ እምነት የቀብር ሥነ-ሥርዓት እና ለተጎጂዎች የጸሎት ዝግጅቶች በከተማው በሚገኙ በርካታ ቤተመቅደሶች እየተከናወኑ ፤ ሃገሪቱ የሦስት የሐዘን ቀናትን ጀምራለች።

የጥቃቱ መንስኤ እስካሁን አልታወቀም። ፖሊስ እንዳለው ከሆነ ግን ካምራብ የአደንዛዥ ዕፅ ከመጠቀም ጋር በተያያዘ በሰኔ ወር ከሥራው እንደተባረረ ተናግሯል።

በሰሜናዊ ምስራቅ ታይላንድ የምትገኘው ይህች ትንሽዬ የገጠር ከተማ ያዘኑትን ቤተሰቦች ለመርዳት እየሞከረች ነው። በርካቶች ደግሞ የጦር መሳሪያዎች ስርጭት መበራከት እና በሃገሪቱ ያለው የአደገኛ ዕፅ ችግርን እያነሱ ይጠይቃሉ።

"ወላጆች ‘ለልጆቻቸው አስተማማኝ ቦታ የት ነው?’ ሲሉ ይጠይቃሉ። በጣም አዝኛለሁ። ባለስልጣናት ደህንነታችንን እንዲያጠናክርልን እማፀናለሁ" ሲሉ የኤሚ አጎት ቬራቻይ ስሪቶንግ ተናግረዋል።