አቡነ ማትያስ ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትግራይ ተጓዙ

የፎቶው ባለመብት, Tigrai Television
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በትግራይ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ከቆመ ከወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀለ ገቡ።
ፓትሪያርኩ ወደ ትግራይ ያቀኑት ከቀናት በፊት በሞት በተለዩት የመቀለ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ዳግማዊ የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ነው።
ዛሬ በመቀለ ከተማ የተገኙት አቡነ ማትያስ በክልሉ የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ምኞታቸን ገልጸዋል።
ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ ትናንት የእረፍታቸው ዜና የተሰማው የብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የአስክሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው በሰጡት ቡራኬ፣ ወደ ክልሉ የተጓዙት የቀብር ሥነ ሥርዓት እና ፍትሃት ለማስፈጸም መሆኑን ተናግረዋል።
አቡነ ማትያስ ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ወደ ትግራይ ሲሄዱ ይህ የመጀመሪያቸው ነው። የክልሉ ሕዝብ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያሳለፈው መከራ ከባድ ነው ያሉት ፓትሪያርኩ አሁን የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ተመኝተዋል።
“እግዚአብሔር አምላክ ከነበረው መከራ ያወጣችሁ የተመሰገነ ይሁን፤ በሰማይ እና በምድር ተዘግቶ፣ በጭንቅ እና በመከራ ውስጥ የነበረው ወገን የሰላም አየር መተንፈስ መጀመሩ ትልቅ ነገር ነው። የእግዚአብሔር ፀጋ ስለሆነ ደስ ሊላችሁ ይገባል። ስለ ሰላም ስንጸልይ ነበር።
“ሰላም በመምጣቱ ደስተኞች ነን፤ ይሄንን እረፍት የሰጠ አምላክ የተመሰገነ ይሁን። ሰላም ትልቅ ነገር ነው፤ በቀላሉ አይገኝም። በሃይማኖት፣ በትህትና፣ በፍቅር እና በፈሪሃ እግዚአብሔር ብቻ ነው የሚገኘው፤ ሰላም በወርቅ እና በእንቁ አይገዛም። አሁን የተመኘነውን ሰላም አግኝተናል እና እግዚአብሔር የጸና ያድርግልን” ብለዋል።
ፓትሪያርኩ በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ የነበረውን አስከፊ ሁኔታ በተመለከተ በይፋ ሲናገሩ የነበረ ሲሆን፣ ሰላም እንዲወርድም በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል። በዚህም ከአንዳንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አመራሮች ተቃውሞን አስተናግደዋል።
በትግራይ ክልል ያሉ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች በጦርነቱ ጊዜ በትግራይ ውስጥ ባሉ ምዕመናን እና አብያተ ክርስቲያናት ላይ የደረሰውን ጉዳት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አላወገዘችም እንዲሁም ጦርነቱን ደግፋችኋል በሚል መለየታቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል።
በዚህም የትግራይ ቤተክህነት መመስረታቸውን በመግለጽ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤትክርስቲያን መለየታቸውን አሳውቀው ነበር።
ደም አፋሳሹ ጦርነትን ያስቆመው የሰላም ስምምነት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ከተፈረመ ከወራት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በትግራይ ካሉ አባቶች ጋር ግንኙቷን ለማሻሻል ፍለጎት እንዳለት በደብዳቤ ገልጻ ነበር።
ነገር ግን በትግራይ ያሉት የሃይማኖቱ መሪዎች ቀደም ሲል ያቀረቧቸውን ምክንያቶች እና ሌሎችንም በመጥቀስ በመለየት ውሳኔያቸው እንደሚቀጥሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ የካቲት 21/2015 ዓ.ም. ማረፋቸው በተገለጸው በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ዳግማዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ወደ መቀለ ዛሬ መቀለ አሉላ አባ ነጋ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ ሲደርሱ በክልሉ ባሉ የሃይማኖት አባቶች ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተዘግቧል።
አቡነ ማትያስ በትግራይ ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከመሳተፍ ባሻገር ሌላ የተያዘላቸው መረሃ ግብር ስለመኖሩ ከጽህፈት ቤታቸው የተባለ ነገር ባይኖርም፣ በክልሉ ካሉ የቤተክርስቲኣኗ አባቶች ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
ፓትሪያርኩ ረቡዕ የካቲት 22/2015 ዓ.ም. ወደ መቀለ የተጓዙበትን የአቡነ ዮሐንስ ዳግማዊ የሽኝት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ምሽት ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን የቤተክርስቲያኗ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።












