የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈፀመ

የፎቶው ባለመብት, Social Media
መስከረም 17/2015 ዓ.ም. ሕይወቱ ያለፈው የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ሐሙስ መስከረም 19/2015 ዓ.ም በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፀመ።
የድምጻዊው የቀብር ሥነ ሥርዓት የተፈፀመው ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹ፣ የሙያ አጋሮቹ ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና በርካታ አድናቂዎቹ በተገኙበት በወዳጅነት ፓርክ የሽኝት ፕሮግራም ከተካሄደ በኋላ ነው።
ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ማክሰኞ ዕለት ጠዋት 1፡30 አካባቢ ወደ ሐኪሙ በመደወል ለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወደሚገኝ ክሊኒክ ከሄደ በኋላ የህመም ማስታገሻዎችና ሌሎች መድኃኒቶችን እንደወሰደ እና 3፡00 አካባቢ ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ መግለጹ ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳሬክተር የሆኑት ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፣ አስክሬኑ ወደ አቤት ሆስፒታል ለምርመራ እንደተወሰደና የምርመራ ውጤቱ ሲታወቅ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ሕልፈቱ በተሰማበት ዕለት ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
እስካሁን ፖሊስ የሞቱን መንስዔ በተመለከተ ይፋ ያደረገው መረጃ የለም።
በድምጻዊው የአስክሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከዚህ ቀደም በድንገት ወደ ጤና ተቋም ሄደው በሕይወት ያልተመለሱ ድምጻውያንን በማስታወስ እና "ህመማቸው ፀንቶ ነው ወይስ የሕክምና ድክመት?" ሲሉ በመጠየቅ፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ተጠይቋል።
የድምጻዊውን ህልፈት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድንና ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም የሙያው አድናቂዎች ሐዘናቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ “ለአገሩ በአጭር እድሜው ብዙ የሠራ ከያኒ ነው” ሲሉ በአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ህልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
በአስክሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የድምጻዊው ወዳጆች በስማቸው የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።
በርካታ አድናቂዎቹም በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Mayor Office of Addis Ababa
ማዲንጎ አፈወርቅ የተወለደው ጎንደር አዘዞ ውስጥ ሲሆን እድገቱ ደብረ ታቦር ነው። እድገቱ በወታደር ቤት መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ባደረጋቸው ቃለ ምልልሶቹ ላይ የገለጸው ማዲንጎ፣ ስሙንም ያገኘው እዚያ መሆኑን ተናግሯል።
ወላጆቹ ያወጡለት ስም ተገኔ የሚል የነበረ ሲሆን፣ ማዲንጎ የሚለውን ስም በወታደር ቤት ሳለ ነበር ያገኘው፤ ከዚያ በኋላ በዚሁ ስም እየተጠራ በሙዚቃ ሙያው እውቅናን አትርፏል።
ከልጅነቱ አንስቶ ለሙዚቃ ከፍተኛ ፍቅር የነበረው ማዲንጎ፣ በጦር ሠራዊት ቤት ሙዚቃ መጫወት ጀምሮ በተለያዩ ክበቦችና የሙዚቃ ባንዶች ጋር በመሆን ሰርቷል።
የታዋቂ ድምጻውያንን ሙዚቃ በመጫወት የጀመረው ማዲንጎ፣ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉለትን የራሱን ነጠላ ሙዚቃዎችና ሙሉ አልበም አቅርቧል።
ማዲንጎ በሥራዎቹ በአገር ውስጥ በታላላቅ መድረኮች ላይ ከሚጋበዙ ድምጻውያን መካከል አንዱ ሲሆን፣ ከአገር ውጪም በተለያዩ አገራት በተደጋጋሚ ሥራዎቹን ሲያቀርብ ቆይቷል።
ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የ44 ዓመት ጎልማሳ እና የአንድ ልጅ አባት ነበር።
ገና በልጅነቱ ዜማ ላስታ የተሰኘውን የሙዚቃ ቡድንን በመቀላቀል የበርካታ እውቅ ድምጻዊያንን ሙዚቃ አስመስሎ በመጫዎት ነበር የበርካቶችን ቀልብ የገዛው።
በዚህም ሥራው የሙዚቃ አታሚዎችን ትኩረት የሳበው ማዲንጎ በ1989 ዓ.ም የመጀመሪያ አልበሙን ‘የፊሸር ባንድ ኮሌክሽን’ የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሙን ከሁለት ጓደኞቹ ጋር አሳትሟል።
በ1991 ዓ.ም የወጣው ‘ስያሜ አጣሁላት’ አልበም ግን በርካታ አድናቂዎች ያገኘበት ሥራው ነበር። ከዚህ አልበም ‘ስያሜ አጣሁላት’ እና ‘አማን ነው ወይ ጎራው’ የተሰኙት ሙዚቃዎቹም ከፍተኛ ዝናን አትርፈውለት ነበር።
ከዚያም በኋላ ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ ጋር እንዲሁም ለብቻው ነጠላ ዜማዎችን አስደምጧል።
በ997 ዓ.ም ‘አይደረግም’ እና በ2007 ዓ.ም ‘ስወድላት’ የተሰኙ አልበሞቹን ያወጣ ሲሆን ከፍተኛ ተወዳጅነትን አግኝተውለታል።
ከዚህም ባሻገር ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸው የሙዚቃ ሥራዎቹን ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ሠርቷል።
“አባይ ወይስ ቬጋስ’ ለተሰኘው ፊልምም የማጀቢያ ሙዚቃ ሥራም ማዲንጎ አሻራውን ካሳረፈባቸው የሙዚቃ ሥራዎች ይጠቀሳል።
ገና በዘጠኝ ዓመቱ የሙዚቃውን ዓለም የተቀላቀለው ድምጻዊው፣ ሕይወቱ ከማለፉ ከሰዓታት በፊት ድረስ ማይክራፎን ከእጁ አልተለየውም ነበር።
ማዲንጎ አፈወርቅ ‘አራራይ የተሰኘ የሙዚቀኞች መረዳጃ እድር’ን ከመሰረቱት መካከልም አንዱ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ በበጎ አድራጎት ሥራዎቹም ይታወሳል።












