ታዋቂው የትግርኛ ድምፃዊ ዳዊት ነጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

ድምፃዊ ዳዊት ነጋ

የፎቶው ባለመብት, Screen Shot

ታትሟል

ታዋቂው ድምጻዊ ዳዊት ነጋ ትናንት እሁድ ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. አመሻሹ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን የቅርብ ወዳጆቹና ዘመዶቹ ለቢቢሲ ገለጹ።

ዳዊት ነጋ ባደረበት ድንገተኛ ህመም ዓርብ ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው አዲስ ህይወት ሆስፒታል መግባቱን ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ሰኞ ዕለት በጉንፋን መልክ የጀመረ ህመሙ ከተባባሰ በኋላ ዓርብ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ እስከ ቅዳሜ ድረስ ህክምና ሲደረግለት ቆይቷል።

ትናንት እሁድ ከሰዓት በኋላ ህመሙ ሲጸናበት ወደ ጽኑ ህሙማን ክትትል ክፍል መግባቱን እና ማታ 1፡00 ሰዓት አካባቢ ህይወቱ ማለፉን ጓደኞቹ እና ዘመዶቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዳዊት ወደ ሆስፒታሉ ከመምጣቱ በፊት ህመሙን ለማስታገስ በቤት ውስጥ ግሉኮስ ይወስድ እንደነበረም ተነግሯል።

ህመሙ ሲበረታበት ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ የስኳር መጠኑ መጨመሩን እና ህመሙ ወደ የሳንባ ምች (ኒሞኒያ) መቀየሩን ተነግሮታል።

በትላንትናው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት በተለየው የዳዊት አስከሬን ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደረግም ሲያስታምሙት የሰነበቱት ጓደኞቹና አብሮ አደጎቹ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ዳዊት ነጋ

የፎቶው ባለመብት, Screen Shot

ዳዊት ማን ነው?

ሚያዝያ 2 1980 ዓ.ም በመቀለ ከተማ የተወለደው ዳዊት ነጋ፣ በአንድ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ ባደረገው ቃለ ምልልስ ወላጆቹ ያረፉት ገና የአስር ዓመት ልጅ እያለ እንደነበረ ተናግሯል።

ገና በለጋነቱ ወላጆቹን አጥቶ የዕለት እንጀራውን ለማግኘት ሲጋራ እና ማስቲካ እንዲሁም ሌሎች ትንንሽ ሸቀጦችን በመቀለ ጎዳናዎች ላይ ይሸጥ ነበር።

ከልጅነቱ ጀምሮ ለሙዚቃ ጥልቅ ፍቅር እንዳደረበት የሚናገረው ዳዊት፣ በ15 ዓመቱ አካባቢ የሙዚቃ ፍላጎቱን እና ህልሙን እውን  ማድረግ በማሰብ “ሰርከስ ትግራይ” በሚባለው የሰርከስና ሙዚቃ ቡድንን በዘፋኝነት ለመቀላቀል ጥያቄ  አቀረበ።

ጥያቄው በጊዜ መልካም ምላሽ ባያገኝም ወደ ማርች ባንድ እንዲቀላቀል እና ከበሮ (ድራም) እንዲጫወት እድል ተሰጠው።

በውስጡ ግን ዘፋኝ የመሆን ፍላጎት እና ህልም ስለ ነበረው ለመዝፈን ከመሞከር አላቆመም።

ዳዊት በቃለ ምልልሱ ላይ "ስኬት ሁልጊዜ በአቅራቢያችን ነው" በማለት “ጠንክረህ ከሰራህ እና ተስፋ ካልቆረጥክ ግቦችህ ላይ መድረስ ከባድ አይደለም” ሲል የራሱን ህይወት በማውሳት ይናገር ነበር።

ዳዊት ነጋ ወላጆቹን ከማጣት ጀምሮ የዕለት ጉርሱን እና የቤት ኪራይ መክፈያ እስከ ማጣት ያሉ የህይወት ፈተናዎችን አሳልፏል።

ከዳዊት ሥራዎች . . . . . .

ዳዊት ነጋ

የፎቶው ባለመብት, Dawit Nega FB

ዳዊት ፈታኙን የህይወት ጉዞ በፅናት እና በትጋት በማሸነፍ ህልሙ ወደነበረው ድምፃዊነት ብቅ ብሎ በልዩ ድምፅ እና ቃና በቀላሉ ብዙዎችን ለመሳብ ችሏል።

ለየት ባለ ድምፁ ዘፍኖ የሚለቃቸው ዘፈኖች በቀላሉ ወደ አድማጭ ጆሮ ደርሰዋል፤ ከትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ባሻገር በሌሎችም ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትንም አግኝቷል።

ከዘፈኖቹ መካከል “ዳኣመና”፣ “ባባ ኢለን”፣ “ሕድያት መቀለ”፣ “ወዛመይ”፣ “ዘዊደሮ”፣ “ብነጸላይ”፣ “ቅዱስ ጸባያ” እና “ቸኮላታ” ይገኙበታል።

ከዓመታት በፊት “ኦሮሚያ” በሚል ርዕስ በትግርኛ፣ ኦሮሚኛና በአማርኛ የሰራው ሙዚቃ ለአድናቂዎቹ ማድረሱም ይታወሳል።

የዘፈኑ ይዘት አንድ ወጣት በአንዲት የኦሮሞ ኮረዳ ፍቅር መሸነፉን እንዲሁም ስለውበቷና ስለማንነቷ ይተርካል።

ድምጻዊ ዳዊት፣ በ2011 አክሱማይት የተሰኘ የሙዚቃ ሰንዱቅ (አልበም) ወደ ሕዝብ አድርሷል።

የመጨረሻው ነጠላ ዜማው "አጆኪ ትግራይ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት ስለተለያዩና መገናኘት ስላልቻሉ የትግራይ ቤተሰቦች ናፍቆት ገልጿል።

ድምፃዊ ዳዊት ነጋ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነበር።