ስደተኛ፡ በዩኬ የስደተኞች ማዕከል ውስጥ መቆየት በመካነ እንስሳት የመኖር ያህል ነው

ታትሟል

በዩናይትድ ኪንደም (ዩኬ) ኬንት በሚገኘው ትልቁ የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ በቅርቡ ሲኖር የነበረ አንድ ስደተኛ በጣቢያው መኖር በመካነ እንስሳት ወይም በእስር ቤት ውስጥ እንደመኖር ነው አለ።

አሕምድ (ስሙ የተቀየረ) ማንስተን ተብሎ በሚጠራው የስደተኞች ጉዳይ ማስፈጸሚያ ጣቢያ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች የሚታዩት እንደ ሰው ሳይሆን እንደ “እንስሳ” ነው ብሏል።

አሕምድ እንደሚለው 130 ሰዎች በአንድ ሰፊ ድንኳን ውስጥ በጋራ ለመኖር ይገደዳሉ።

በአሁኑ ሰዓት 1600 ሰዎችን ማስተናገድ ባለበት ጣቢያ ከ4ሺህ በላይ ስደተኞች ታጭቀውበት ይገኛሉ።

የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ ግን ለስደተኞቹ የሚያስፈልገውን “ሠረታዊ ፍላጎት” እያሟላሁ ነው ይላል።

የኢሚግሬሽን ሚኒስትሩ ሮበርት ጄነሪክ ከዚህ ቀደም በጣቢያው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር በጊዜ ሂደት እየቀነሰ ነው ብለው ነበር።

ከሦስት ቀናት በፊት ከስደተኛ መጠለያ ጣቢያው የወጣው አሕመድ በማንስተን 24 ቀናትን አሳልፏል። በዚህ ቆይታው ወለል ላይ እንዲተኛ መገደዱን፣ ወደ መጸዳጃ ቤት እንዳይሄድ መከልከሉን፣ ገላውን መታጠብም ሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወደ ውጪ ከመውጣት መታገዱን ተናግሯል።

የተሻለ ነጻነት እና ሕይወት ፍለጋ ከኢራን መውጣቱን የሚናገረው አሕመድ፤ በጣቢያው ያሉ ሰዎች በትውልድ አገራቸው የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር ደውለው ዩናይትድ ኪንገድም መድረሳቸውን እንዳይናገሩ እንደሚከለከሉም ጨምሮ ተናግሯል።

“ባለፉት 24 ቀናት እዚያ ነበርኩ። ቤተሰቦቼ ልሙት በሕይወት ልኑር የሚያውቁት ነገር የለም። ስለ እኔ የሚያውቁት አንድም ነገር የለም” ይላል።

“እዚያ ያሉት ሰዎች በሙሉ ቤተሰብ አላቸው። ስላለንበት ሁኔታ ማወቅ አለባቸው” በማለት ስደተኞች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ ስለመደረጋቸው አስረድቷል።

የቀድሞ የጦር ሰፈር ማንስተን የስደተኞች ጉዳይ ማስፈጸሚያ ሆኖ የተቋቋመው ከወራት በፊት ነበር። በአሁኑ ወቅት በፈረንሳይ በኩል አድርገው በአነስተኛ ጀልባዎች የኢንግሊሽ ቻናልን አቋርጠው ዩኬ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ጨምሯል።

ይህ ጣቢያ የተከፈተው ስደተኞች ማንታቸው እስኪረጋገጥ እና የሚደረግባቸው የደኅንነት ምርመራ እስኪጠናቀቅ ለጥቂት ቀናት በሚል ነበር።

በመቀጠል ወደ የአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮ የጥገኝነት ጠያቂዎች መኖሪያ ይሸጋገራሉ። በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ የጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን ተከትሎ የጥገኝነት ጠያቂዎች መቆያ ሆቴሎች ሆነው ቀጥለዋል።

ከማንስተን በተጨማሪ በኬንት በሚገኝ እና ስሙ ባልተጠቀሰ የስደተኞች ማቆያ ጣቢያ ውስጥ ከአሳዳጊዎቻቸው የተነጠሉ ሕጻናት ወለል ላይ እንዲተኙ ሲገደዱ የሚያሳይ ምስል ለቢቢሲ ደርሷል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮ ቃል አቀባይ ማንስተን የስደተኞችን ጉዳይ ለማስፈጸም የተሟላ አቅም እንዳለው ገልጸው በከፍተኛ ቁጥር በአነስተኛ ጀልባዎች በርካታ ስደተኞች ወደ ዩኬ መግባታቸው በመንግሥት ላይ ጫና መፍጠሩን እና በቢሊዮን የሚቆጠር የግብር ከፋዮች ገንዘብ በየዕለቱ ወጪ እንደሚሆን ተናግረዋል።