የአፍሪካ ኅብረት እየተካሄደ ስላለው የሰላም ንግግር የተደረሰበትን ዛሬ ያሳውቃል

ታትሟል

በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለቀናት ሲካሄድ የቆየውን የሰላም ንግግር አስመልክቶ የደረሰበትን ደረጃ የአፍሪካ ኅብረት በዛሬው ዕለት፣ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም እንደሚያሳውቅ ተገለጸ።

በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የሚደረገውን የሰላም ንግግር የአንድ ሳምንት ቆይታን አስመልክቶም አንዱ አሸማጋይ የሆኑት የኅብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴንጉን ኦቦሳንጆ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሏል።

ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት የሚደረገውን ድርድር አስመልክቶም ዛሬ ረቡዕ በፕሪቶሪያ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ይሰጣሉ።

የመጠናቀቂያ ጊዜው ተራዝሞ አስከዛሬ የዘለቀው ንግግርን በተመለከተ መግለጫው ፕሪቶሪያ ውስጥ በሚገኘው ዲርኮ ኮንፍረንስ ማዕከል እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ኃይሎች መከካከል የሚካሄደው የሰላም ንግግር ማክሰኞ ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን እሁድ ጥቅምት 20/2015 ዓ.ም ይጠናቀቃልም ተብሎ ነበር።

ሆኖም የቢቢሲ ምንጮች እስከዛሬ ጥቅምት 23 ድረስ ለተጨማሪ ቀናት መራዘሙን ገልጸው ነበር።

የሰላም ንግግሩን በተመለከተ አስካሁን ከየትኛውም ወገን ምንም አይነት ፍንጭ ሳይሰጥ በምስጢራዊነት የተያዘ ሲሆን ከሚዲያም አይን ርቆ እየተካሄደ ይገኛል።

በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ ከተማ በሚገኘው የአገሪቱ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር መሥሪያ ቤት (የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት) ውስጥ እየተካሄደ ባለው ንግግር፣ ከሁለቱም ወገን ከፍተኛ ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

ሁለቱ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት በዝግ ስብሰባቸውን እያደረጉ የሚገኙ ሲሆን እስካሁን የድርድሩ አጀንዳዎችም ሆነ የሰላም ንግግሩ ሂደት የደረሰበት ደረጃ ምን እንደሆነ አይታወቅም።

አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች በደቡብ አፍሪካ እያደረጉት ያሉት ውይይት አንዱ ዓላማ የኤርትራን ጦር ከሰሜን ኢትዮጵያ ማስወጣት እንደሆነ ማስታወቁ ይታወሳል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ሰኞ ጥቅምት 21/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ላይ የእርስ በርስ ጦርነቱ ተፋላሚዎች የሚካሂዱት ንግግር አራት ግቦችን ለማሳካት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ የውይይቱ አላማዎች ናቸው ብለው የጠቀሷቸው፤ በአስቸኳይ ግጭት ማቆም፣ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ ማቅረብ፣ የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ እና የኤርትራን ጦር ከሰሜን ኢትዮጵያ ማስወጣት ነው ብለዋል።

የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች የሚያደርጉትን ድርድር በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፑምዚሌ ማላምቦ-ናኩክ እንደሚያስተባብሩት ከዚህ ቀደም ተገልጿል።

አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) ደግሞ በድርድሩ ላይ የታዛቢነት ሚና ኖሯቸው ተሳታፊ እንደሚሆኑ የአፍሪካ ኅብረት አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ለቻይና ዓለም አቀፍ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ተስፋ እንዳለ አመልክተዋል። ሆኖም በሰላም ንግግሩ ውስጥ "የውጭ ጣልቃ ገብነት ከግራም ከቀኝም የሚኖር ከሆነ ፈታኝ ይሆናል" ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ሁለት ዓመት የሆነው ጦርነት ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመትን አስከትሏል።

የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት እና አሜሪካ ጦርነቱ በንግግር መቋጫ እንዲያገኝ ለረጅም ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።