ካናዳዊው ታዳጊ ፖሊሶች ላይ ተኩስ ከፍቶ ሁለቱን ገደለ

ታትሟል

በምዕራባዊቷ የካናዳ ግዛት አልበርታ ውስጥ በቤተሰብ መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት የተጠሩ ሁለት ፖሊሶችን አንድ ታዳጊ ተኩሶ መግደሉ ተዘገበ።

የኤድመንተን ከተማ ፖሊስ እንዳስታወቀው ፖሊሶቹን ተኩሶ ገድሏል የተባለው ተጠርጣሪ የ16 ዓመት ታዳጊ ሲሆን፣ ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ እራሱን በጥይት መትቶ መግደሉን ፖሊስ ገልጿል።

የ55 ዓመቷ የታዳጊው እናትም በጥይት ተመትተው ለሕይወታቸው አስጊ የሆነ ጉዳት ስለደረሰባቸው ሆስፒታል ተወስደዋል።

በታዳጊው የተገደሉት ሁለቱ ፖሊሶች የ30 እና የ35 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሲሆን፣ ከአምስት አስከ ስምንት ዓመት በፖሊስ ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው ተብሏል።

ፖሊሶቹ ጥቃቱ ወደ ተፈጸመበት አፓርትመንት የሄዱት በቤተሰብ መካከል በተነሳ ግጭት መካከል ጣልቃ እንዲገቡ የታዳጊው እናት ባደረጉት የስልክ ጥሪ መሠረት መሆኑን የፖሊሶቹ አዛዥ ዴል ማክፊ ተናግረዋል።

ከስፍራው እንደደረሱም እናትየውን ከህንጻው ውጪ ያገኟቸው ሲሆን፣ ወደ ህንጻው እየተቃረቡ ሳለ ነበር ታዳጊው በፖሊስ መኮንኖቹ ላይ በርካታ ጥይቶችን በመተኮስ የመታቸው።

ፖሊሶቹ በተጠሩበት ጊዜ በግጭቱ ውስጥ የታጠቀ ሰው ስለመኖሩ መረጃ አልነበራቸውም። በዚህም ምክንያት እራሳቸውን ለመከላከል ሙከራ እንኳን የሚያደርጉበት ዕድል ሳያገኙ በታዳጊው ተተኩሶባቸው መገደላቸውን የፖሊስ ባለሥልጣን ገልጸዋል።

ከዚያም በኋላ ተጠርጣሪው እና እናቱ ጭቅጭቅ ውስጥ ገብተው ታዳጊው እናቱን ተኩሶ ክፉኛ አቁስሏል።

ፖሊስ የተጠርጣሪውን እና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ነገር ግን በደህና ሁኔታ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙትን እናት ማንነት በተመለከተ እስካሁን ምንም መረጃ አልሰጠም።

የፖሊስ ባለሥልጣናት እንዳሉት ከዚህ በፊት “ጥቃት በሌለበት” የአእምሮ ጤና ክስትት ምክንያት ፖሊሶች ተጠርተው ወደ እዚሁ ቤተሰብ በመሄዳቸው የታዳጊው ሁኔታ በፖሊስ የሚታወቅ ነበር።

ፖሊስ ተጠርጣሪውን፣ የተጠቀመበትን የጦር መሳሪያ እና ዝርዝር ጉዳዮችን ያልገለጸ ሲሆን፣ በጥቃቱ ዙሪያ ተጨማሪ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።

የፖሊሶቹን መገደል ተከትሎ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶን ጨምሮ በርካታ ካናዳውያን ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው።

የፖሊስ መኮንኖች የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ የእራሳቸውን ሕይወት ለአደጋ እንደሚያጋልጡ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ አስፍረዋል።

“በሥራ ላይ እያሉ የተገደሉት ሁለት ፖሊሶችም ይህንን እውነታ ያረጋግጣሉ” በማለት የተሰማቸውን ሐዘን ለፖሊሶቹ ቤተሰቦች እና ለባልደረቦቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው “ከጎናችሁ ነን” ብለዋል።

የኤድመንተን ከተማ ከንቲባ አማርዬት ሶሂ በበኩላቸው በፖሊሶቹ ላይ የተፈጸመው ግድያን “በጣም አስቸጋሪ እና አሳዛኝ” ሲሉ ገልጸውታል።

የአሁኖቹን ጨምሮ ባለፉት ስድስት ወራት ካናዳ ውስጥ ስምነት ፖሊሶች በሥራ ላይ እንዳሉ ተገድለዋል። ከአልበርታዋ ኤድመንተን ውጪ ሌሎቹ ፖሊሶች የተገደሉት በኦንታሪዮ እና በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ግዛት ውስጥ ነው።