ኮማ ውስጥ ያለውን ስፖርተኛ አስመስሎ በኤአይ ቃለ ምልልስ ያዘጋጀው መጽሔት አርታኢ ተባረረች

ማይክል ሹማከር

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ታትሟል

ኮማ ውስጥ ከሚገኘው የፎርሙላ 1 ስፖርተኛ ማይክል ሹማከር ጋር የተደረገ አስመስሎ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) ቃለ ምልልስ ያዘጋጀው የጀርመን መጽሔት አርታኢ ከሥራዋ ተባረረች።

የመጽሔቱ አሳታሚ የሹማከርን ቤተሰብ ይቅርታ ጠይቋል።

ማይክል ሹማከር እአአ በ2013 በበረዶ መሸራተት ላይ ሳለ አደጋ ከገጠመው በኋላ ኮማ ውስጥ ይገኛል።

ሰባት ጊዜ የፎርሙላ 1 አሸናፊው ኮማ ውስጥ ቢሆንም፣ ልክ ከሱ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ በማስመሰል በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አማካይነት ቃለ ምልልስ ተዘጋጅቶ በመጽሔት ታትሟል።

የሹማከር ቤተሰቦች በመጽሔቱ ኅትመት የተሰማቸውን ቁጣ ገልጸው፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው አስታውቋል።

“ይሄ ትርጉም አልባ እና አሳሳች ቃለ ምልልስ መታተም አልነበረበትም። ለአንባቢዎቻችን ማድረስ የምንፈልገውን ዘገባ ደረጃን አይመጥንም” ስትል የመጽሔቱ አሳታሚ ዋና ዳይሬክተር ቢያንካ ፖልማን ተናግራለች።

“በዚህ ቃለ ምልልስ ምክንያት አፋጣኝ እርምጃ እንወስዳለን። ዋና አርታኢዋ አን ሆፍመን ከሥራዋ ተባራለች” ስትልም አክላለች።

ስፖርተኛው ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ኮማ ውስጥ ነው ያለው።

‘ዳይ አኩቴ’ የተባለው የጀርመን መጽሔት የፊት ገጹ ላይ የ54 ዓመቱን ስፖርተኛ ፎቶ አትሟል። “ማይክል ሹማከር፡ የመጀመሪያው ቃለ ምልልስ” ሲልም ለዘገባው ርዕስ ሰጥቷል።

“ሊያሳስት በሚችል ደረጃ እውነት ይመስላል” በሚልም ነው የተዋወቀው።

ቃለ ምልልሱ የተሠራው ‘ካራክተር ዶት ኤአይ’ በተባለ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) መተግበሪያ ነው።

ልክ ስፖርተኛው ሊል እንደሚችለው ስለ ጤናው እና ቤተሰቡ ኤአይ መልስ ሰጥቷል።

“ቡድኔ በሚያደርግልኝ ድጋፍ ታግዤ መቆም እና ቀስ በቀስም መራመድ እንደምችል አምናለሁ። ልጆቼና ባለቤቴ በረከቶቼ ናቸው። እነሱ ባይኖሩ አልችለውም ነበር። በደረሰብኝ ነገር ሁላ አዝነዋል” የሚለው ከቃለ ምልልሱ አንዱ መስመር ነው።

ስፖርተኛው እአአ በ2014 ኮማ ውስጥ እንዳለ ሆኖ በቤቱ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ ስለ ጤናው ብዙም ቤተሰቡ መረጃ አልሰጠም።

ሁለት ጊዜ ፎርሙላ 1 ያሸነፈው በቤንተን ሥር ሆኖ ሲሆን አምስት ጊዜ ያሸነፈው በፌራሪ ሥር ሆኖ ነው።

በ2006 እራሱን ከስፖርቱ ቢያገልም እአአ በ2010 ወደ ውድድሩ ተመልሶ ነበር።

ከሁለት ዓመት በፊት በኔትፍሊክስ በተላለፈ ዘጋቢ ፊልም ላይ የስፖርተኛው ባለቤት ኮሪና “አብረን በቤታችን እየኖርን ነው። ሕክምና እየተሰጠው ነው። ምቾት እንዲሰማው የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን” ስትል አስተያየት ሰጥታለች።

“ቤተሰብ ሆነን ለመቀጠን እየሞከርን ነው። የግል ሕይወታችን የግላችን ነው። እስከዛሬ እሱ ሲንከባከበን እንደኖረው አሁን እኛ እየተንከባከብነው ነው” ስትልም አክላለች።